መዝሙር 58 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 58 ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤ የዳዊት ሚክታም ። 1 ኀያላን ሆይ፤ በውኑ ጽድቅ ከአፋችሁ ይወጣል? የሰው ልጆች ሆይ፤ በቅን ትፈርዳላችሁን? 2 የለም፤ በልባችሁ ክፋትን ታውጠነጥናላችሁ፤ በእጃችሁም ዐመፅን በምድር ላይ ትጐነጕናላችሁ። 3 ክፉዎች በማሕፀን ሳሉ ከመንገድ የወጡ ናቸው፤ ሲወለዱ ጀምሮ የተሳሳቱና ውሸታሞች ናቸው። 4 መርዛቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፤ አልሰማ ብላ ጆሮዋን እንደ ደፈነች እፉኝት ናቸው፤ 5 ጆሮዋንም የደፈነችው የመተተኛውን ወይም የጠቢቡን ደጋሚ ቃል ላለመስማት ነው። 6 አምላክ ሆይ፤ ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ስበር፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንበሶቹን መንጋጋ አወላልቅ! 7 ፈጥኖ እንደሚያልፍ ወራጅ ውሃ ይጥፉ፤ ቀስታቸውን ሲስቡ ፍላጻቸው ዱልዱም ይሁን። 8 ሲሄድ እንደሚቀልጥ ቀንድ አውጣ ይሁኑ፤ ፀሓይን እንደማያይ ጭንጋፍ ይሁኑ። 9 የእሾኽ እሳት ገና ድስታችሁን ሳያሰማው፣ ርጥቡንም ደረቁንም እኩል በዐውሎ ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል። 10 ጻድቃን በቀልን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ እግራቸውንም በግፈኞች ደም ይታጠባሉ። 11 ሰዎችም፣ “በርግጥ ለጻድቃን ብድራት ተቀምጦላቸዋል፤ በእውነትም በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ” ይላሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.