መዝሙር 49 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 49 ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 እናንተ ሕዝቦች ሁላችሁ፤ ይህን ስሙ፤ በዓለም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አድምጡ። 2 ዝቅተኞችና ከፍተኞች፣ ባለጠጎችና ድኾች ይህን በአንድነት ስሙ። 3 አፌ የጥበብን ቃል ይናገራል፤ የልቤም ሐሳብ ማስተዋልን ይሰጣል። 4 ጆሮዬን ወደ ምሳሌ አዘነብላለሁ፤ እንቆቅልሼንም በበገና እፈታለሁ። 5 የአጭበርባሪዎች ክፋት በከበበኝ ጊዜ፣ በክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ? 6 በሀብታቸው የሚመኩትን፣ በብልጽግናቸውም የሚታመኑትን ለምን እፈራለሁ? 7 የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው፣ ወይም ለእግዚአብሔር ወጆ የሚከፍልለት ማንም የለም። 8 የነፍስ ቤዛ ውድ ነውና፤ በቂ ዋጋም ከቶ ሊገኝለት አይችልም፤ 9 በዚህም ዘላለም ይኖራል፣ መበስበስንም አያይም። 10 ጠቢባን ሟቾች መሆናቸው የሚታይ ነው፤ ሞኝና ደነዝም ይጠፋሉ፤ ጥሪታቸውንም ለሌላው ጥለው ይሄዳሉ። 11 መሬቶችን በስማቸው ቢሰይሙም፣ መቃብራቸው የዘላለም ቤታቸው፣ ከትውልድ እስከ ትውልድም መኖሪያቸው ይሆናል። 12 ሰው በሀብቱ እንደ ተከበረ አይዘልቅም፤ ታይተው የሚጠፉ እንስሳትን ይመስላል። 13 ይህ የተላላዎች ዕድል ፈንታ፣ የእነርሱንም አባባል ተቀብለው ለሚከተሏቸው፣ መጨረሻ ግብ ነው። ሴላ 14 እንደ በጎች ለሲኦል የተዳረጉ ናቸው፤ ሞትም እረኛቸው ይሆናል፤ ቅኖች በማለዳ ይገዟቸዋል፤ አካላቸው ከክብር ቤታቸው ርቆ፣ በሲኦል ይፈራርሳል። 15 እግዚአብሔር ግን ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል፤ በርግጥም ይወስደኛል። ሴላ 16 ሰው ባለጠጋ ሲሆን፣ የቤቱም ክብር ሲበዛለት አትፍራ፤ 17 በሚሞትበትም ጊዜ ይዞት የሚሄደው አንዳች የለምና፤ ክብሩም ዐብሮት አይወርድም። 18 በሕይወት ሳለ ራሱን እንደ ተባረከ ቢቈጥርም፣ ሰዎች በበለጸግህ ጊዜ ቢያወድሱህም፣ 19 ብርሃን ከቶ ወደማያዩት፣ ወደ አባቶች ማኅበር ይቀላቀላል። 20 ሰው በሀብቱ እንደ ተከበረ አይዘልቅም፤ ታይተው የሚጠፉ እንስሳትን ይመስላል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.