መዝሙር 48 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 48 ዝማሬ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰው ተራራ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባዋል። 2 የምድር ሁሉ ደስታ የሆነው፣ በሰሜን በኩል በርቀት የሚታየው፣ በከፍታ ላይ አምሮ የደመቀው የጽዮን ተራራ፣ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነው። 3 እግዚአብሔር በአዳራሾቿ ውስጥ ሆኖ፣ ብርቱ ምሽግ እንደ ሆናት አስመስክሯል። 4 እነሆ፤ ነገሥታት ተባብረው መጡ፤ አንድ ላይ ሆነውም ገሠገሡ። 5 አይተውም ተደነቁ፤ ደንግጠውም ፈረጠጡ። 6 ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣ በዚያ ብርክ ያዛቸው። 7 የምሥራቅ ነፋስ የተርሴስን መርከብ እንደሚሰባብር፣ አንተ አብረከረክሃቸው። 8 እንደ ሰማን፣ በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ከተማ፣ በአምላካችን ከተማ፣ እንዲሁ አየን፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ያጸናታል። ሴላ 9 አምላክ ሆይ፤ በቤተ መቅደስህ ውስጥ ሆነን፣ ምሕረትህን እናስባለን። 10 አምላክ ሆይ፤ ምስጋናህ እንደ ስምህ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ይዘልቃል፤ ቀኝ እጅህም ጽድቅን የተሞላች ናት። 11 ስለ ፍርድህ፣ የጽዮን ተራራ ሐሤት ታድርግ፤ የይሁዳ መንደሮችም ደስ ይበላቸው። 12 በጽዮን አካባቢ ተመላለሱ፤ ዙሪያዋንም ሂዱ፤ የጥበቃ ግንቦቿንም ቍጠሩ፤ 13 ለሚቀጥለው ትውልድ ትናገሩ ዘንድ፣ መከላከያ ዕርዶቿን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ መጠበቂያ ማማዎቿን እዩ። 14 ይህ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችን ነውና፤ እስከ መጨረሻው የሚመራንም እርሱ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.