መዝሙር 39 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 39 ለመዘምራን አለቃ፣ ለኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እኔ፣ “በአንደበቴ እንዳልበድል፣ መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ክፉዎችም በእኔ ዘንድ እስካሉ ድረስ፣ ልጓም በአፌ አስገባለሁ” አልሁ። 2 እንደ ዲዳ ዝም አልሁ፤ ለበጎ ነገር እንኳ አፌን ዘጋሁ፤ ሆኖም ጭንቀቴ ባሰ። 3 ልቤ በውስጤ ጋለ፤ በማሰላስልበትም ጊዜ እሳቱ ነደደ፤ ከዚያም በአንደበቴ እንዲህ ተናገርሁ፤ 4 “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሕይወቴን ፍጻሜ፣ የዘመኔንም ቍጥር አስታውቀኝ፤ ዐላፊ ጠፊ መሆኑንም ልረዳ። 5 እነሆ፤ ዘመኔን በስንዝር ለክተህ አስቀመጥህ፤ ዕድሜዬም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው፤ በርግጥ የሰው ሁሉ ሕይወት ተን ነው። ሴላ 6 “ሰው የጥላ ውልብታ ነው፤ በከንቱም ይታወካል፤ ለማን እንደሚሆን ሳያውቅ ሀብት ንብረት ያከማቻል። 7 “ጌታ ሆይ፤ አሁንስ ወደ ማን ልመልከት? ተስፋዬ በአንተ ላይ ነው። 8 ከኀጢአቴ ሁሉ አድነኝ፤ የሞኞች መሣለቂያ አታድርገኝ። 9 ይህን ያደረግህ አንተ ነህና፣ ዝም እላለሁ፤ አፌንም አልከፍትም። 10 ክንድህን አንሣልኝ፤ ከእጅህ ምት የተነሣ ደክሜአለሁ። 11 ሰዎችን ስለ ኀጢአታቸው ለመቅጣት ትገሥጻቸዋለህ፤ ሀብታቸውንም ብል እንደ በላው ታደርጋለህ፤ በርግጥ ሰው ሁሉ ተን ብቻ ነው። ሴላ 12 “እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴን አድምጥ፤ ልቅሶዬንም ቸል አትበል፤ በአንተ ፊት እኔ መጻተኛ ነኝና፤ እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝ። 13 ላለመመለስ ከመሰናበቴ በፊት፣ ዳግመኛ ደስ ይለኝ ዘንድ ዐይንህን ከላዬ አንሣ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.