መዝሙር 38 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 38 የዳዊት መዝሙር፤ ለመታሰቢያ። 1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በቍጣህ አትገሥጸኝ፤ በመዓትህም አትቅጣኝ። 2 ፍላጻዎችህ ወግተውኛልና፤ እጅህም ተጭናኛለች። 3 ከቍጣህ የተነሣ ሰውነቴ ጤና አጥቷል፤ ከኀጢአቴም የተነሣ ዐጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። 4 በደሌ ውጦኛል፤ እንደ ከባድ ሸክምም ተጭኖኛል። 5 ከቂልነቴ የተነሣ፣ ቍስሌ ሸተተ፤ መገለም፤ 6 ዐንገቴን ደፋሁ፤ ጐበጥሁም፤ ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ። 7 ወገቤ እንደ እሳት ነድዷል፤ ሰውነቴም ጤና የለውም። 8 እጅግ ዝያለሁ፤ ፈጽሞም ደቅቄአለሁ፤ ከልቤም መታወክ የተነሣ እጮኻለሁ። 9 ጌታ ሆይ፤ ምኞቴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነው፤ ጭንቀቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም። 10 ልቤ በኀይል ይመታል፤ ጕልበት ከድቶኛል፤ የዐይኔም ብርሃን ጠፍቷል። 11 ከቍስሌ የተነሣ ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ሸሹኝ፤ ጎረቤቶቼም ርቀው ቆሙ። 12 ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ሊያጠፉኝ ዛቱ፤ ቀኑንም ሙሉ ተንኰል ይሸርባሉ። 13 እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቈሮ፣ አፉንም መክፈት እንደማይችል ዲዳ ሆንሁ። 14 በርግጥም ጆሮው እንደማይሰማ፣ አንደበቱም መልስ መስጠት እንደማይችል ሰው ሆንሁ። 15 እግዚአብሔር ሆይ፤ በተስፋ እጠብቅሃለሁ፤ ጌታ አምላኬ ሆይ፤ አንተ መልስ ትሰጠኛለህ። 16 እኔ፣ “ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ አይበላቸው፤ እግሬም ሲንሸራተት፣ በላዬ አይኵራሩብኝ” ብያለሁና። 17 ልወድቅ ተቃርቤአለሁ፤ ከሥቃዬም ከቶ አልተላቀቅሁም። 18 በደሌን እናዘዛለሁ፤ ኀጢአቴም አውካኛለች። 19 ብርቱዎች ጠላቶቼ ብዙ ናቸው፤ ያለ ምክንያት የሚጠሉኝም ስፍር ቍጥር የላቸውም። 20 መልካሙን ስለ ተከተልሁ፣ በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልሱልኝ ከሰሱኝ። 21 እግዚአብሔር ሆይ፤ አትተወኝ፤ አምላኬ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ። 22 ጌታዬ መድኅኔ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.