Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መዝሙር 33 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 33

1 ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ቅኖች ሊወድሱት ይገባቸዋል።

2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፤ ዐሥር አውታር ባለውም በገና ዘምሩለት።

3 አዲስ መዝሙር ዘምሩለት፤ በገናውን ባማረ ቅኝት ደርድሩ፤ እልልም በሉ።

4 የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነውና፤ የሚሠራውም ሁሉ የታመነ ነው።

5 እግዚአብሔር ጽድቅንና ፍትሕን ይወድዳል፤ ምድርም በምሕረቱ የተሞላች ናት።

6 በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ተሠሩ፤ በአፉም እስትንፋስ የከዋክብት ሰራዊት።

7 የባሕርን ውሃ በአንድ ዕቃ ይሰበስባል፤ ቀላዩንም በአንድ ስፍራ ያከማቻል።

8 ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፤ በዓለም የሚኖር ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ይንቀጥቀጥ።

9 እርሱ ተናግሯልና ሆኑ፤ አዝዟልና ጸኑም።

10 እግዚአብሔር የሕዝቦችን ምክክር ከንቱ ያደርጋል፤ የሕዝብንም ዕቅድ ያጨናግፋል።

11 የእግዚአብሔር ሐሳብ ግን ለዘላለም ይጸናል፤ የልቡም ሐሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው።

12 ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነው ሕዝብ፣ ለርስቱ የመረጠውም ወገን፤

13 እግዚአብሔር ከሰማይ ይመለከታል፤ የሰውንም ልጆች ሁሉ ያያል፤

14 ከማደሪያው ቦታ ሆኖ፣ በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ይመለከታል፤

15 እርሱ የሁሉን ልብ የሠራ፣ የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያስተውል ነው።

16 ንጉሥ በሰራዊቱ ታላቅነት አይድንም፤ ጀግናም በኀይሉ ብርታት አያመልጥም።

17 በፈረስ ድል አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ተስፋ ነው፤ በብርቱ ጕልበቱም ማንንም አያድንም።

18 እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤ ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኵረዋል።

19 በዚህም ነፍሳቸውን ከሞት ያድናል፤ በራብ ዘመንም በሕይወት ያኖራቸዋል።

20 ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤ እርሱ ረዳታችንና ጋሻችን ነው።

21 ልባችን በርሱ ደስ ይለዋል፤ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና።

22 እግዚአብሔር ሆይ፤ ተስፋ ባደረግንህ፣ በእኛ ላይ ምሕረትህ ትሁን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告