Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መዝሙር 28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 28
የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤ አንተ ዝም ካልኸኝ፤ ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ።

2 ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣ እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣ የልመናዬን ቃል ስማ።

3 በልባቸው ተንኰል እያለ፣ ከባልንጀሮቻቸው ጋራ በሰላም ከሚናገሩ፣ ከክፉ አድራጊዎችና ከዐመፃ ሰዎች ጋራ ጐትተህ አትውሰደኝ።

4 እንደ ሥራቸው፣ እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤ እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤ አጸፋውን መልስላቸው።

5 ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ ስለሌላቸው፣ ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣ እርሱ ያፈርሳቸዋል፤ መልሶም አይገነባቸውም።

6 የልመናዬን ቃል ሰምቷልና፣ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን።

7 እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤ ልቤ ሐሤት አደረገ፤ በዝማሬም አመሰግነዋለሁ።

8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታታቸው ነው፤ ለቀባውም የመዳን ዐምባ ነው።

9 ሕዝብህን አድን፤ ርስትህንም ባርክ፤ እረኛ ሁናቸው፤ ለዘላለሙም ዐቅፈህ ያዛቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告