መዝሙር 142 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 142 ዋሻ ውስጥ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት ማስኪል፤ ጸሎት። 1 ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር ልመና አቀርባለሁ። 2 ብሶቴን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ ችግሬንም በፊቱ እናገራለሁ። 3 መንፈሴ በውስጤ ሲዝል፣ መንገዴን የምታውቅ አንተ ነህ፤ በመተላለፊያ መንገዴ ላይ፣ ወጥመድ በስውር ዘርግተውብኛል። 4 ወደ ቀኜ ተመልከት፤ እይም፤ ስለ እኔ የሚገድደው የለም፤ ማምለጫም የለኝም፤ ስለ ነፍሴም ደንታ ያለው የለም። 5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ደግሞም፣ “አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ በሕያዋንም ምድር ዕድል ፈንታዬ ነህ” እላለሁ። 6 እጅግ ተስፋ ቈርጫለሁና፣ ጩኸቴን ስማ፤ ከዐቅም በላይ ሆነውብኛልና፣ ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። 7 ስምህን አመሰግን ዘንድ፣ ነፍሴን ከእስር አውጣት፤ ከምታደርግልኝም በጎ ነገር የተነሣ፣ ጻድቃን በዙሪያዬ ይሰበሰባሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.