መዝሙር 115 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 115 115፥4-11 ተጓ ምብ – መዝ 135፥15-20 1 ለእኛ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለእኛ ሳይሆን፣ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ፣ ለስምህ ክብርን ስጥ። 2 አሕዛብ፣ “አምላካቸው የት አለ?” ለምን ይበሉ? 3 አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል። 4 የእነርሱ ጣዖታት ግን የሰው እጅ ያበጃቸው፣ ብርና ወርቅ ናቸው። 5 አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፣ 6 ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው፤ አያሸትቱም፤ 7 እጅ አላቸው፤ አይዳስሱም፤ እግር አላቸው፤ አይሄዱም፤ በጕሮሯቸውም ድምፅ አይፈጥሩም። 8 እነዚህን የሚያበጁ፣ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ። 9 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረዳታቸውና ጋሻቸው እርሱ ነው። 10 የአሮን ቤት ሆይ፤ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረዳታቸውና ጋሻቸው እርሱ ነው። 11 እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረዳታቸውና ጋሻቸው እርሱ ነው። 12 እግዚአብሔር ያስበናል፤ ይባርከናልም፤ እርሱ የእስራኤልን ቤት ይባርካል፤ የአሮንንም ቤት ይባርካል። 13 እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ሁሉ፣ ትልቁንም ትንሹንም ይባርካል። 14 እግዚአብሔር እናንተንና ልጆቻችሁን፣ በባርኮቱ ያብዛችሁ። 15 ሰማይንና ምድርን በፈጠረ፣ በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። 16 ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት። 17 እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑት የሞቱት አይደሉም፤ ወደ ዝምታው ዓለም የሚወርዱም አይደሉም። 18 ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔርን የምንባርክ እኛ ነን። እግዚአብሔር ይመስገን። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.