Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ምሳሌ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የጥበብ ጥሪ

1 ጥበብ ጮኻ አትጣራምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አታሰማምን?

2 በመንገድ አጠገብ ባሉ ኰረብቶች፣ መንገዶቹ በሚገናኙበትም ላይ ትቆማለች፤

3 ወደ ከተማዪቱ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣ በመግቢያዎቹ ላይ፣ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ ስትል ትጮኻለች፤

4 “ሰዎች ሆይ፤ የምጠራው እኮ እናንተን ነው፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ድምፄን ከፍ አደርጋለሁ።

5 እናንተ አላዋቂዎች፤ ጠንቃቃነትን ገንዘብ አድርጉ፤ እናንተ ሞኞች፤ ማስተዋልን አትርፉ።

6 የምናገረው ጠቃሚ ነገር ስላለኝ አድምጡኝ፤ ቀና ነገር ለመናገር ከንፈሮቼን እከፍታለሁ።

7 አንደበቴ እውነትን ይናገራል፤ ከንፈሮቼ ክፋትን ይጸየፋሉና።

8 ከአንደበቴ የሚወጡት ቃሎች ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ አንዳቸውም ጠማማና ግራ የሚያጋቡ አይደሉም።

9 በጥልቅ ለሚያስተውሉ ሁሉም ቀና ናቸው፤ ዕውቀት ላላቸውም ስሕተት የለባቸውም።

10 ከብር ይልቅ ምክሬን፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ፤

11 ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናትና፤ ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም።

12 “እኔ ጥበብ ከማስተዋል ጋራ አብሬ እኖራለሁ፤ ዕውቀትና ልባምነት ገንዘቦቼ ናቸው።

13 እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፤ እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣ ክፉ ጠባይንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።

14 ምክርና ትክክለኛ ጥበብ የእኔ ናቸው፤ ማስተዋል አለኝ፤ ብርታት አለኝ።

15 ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤ ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤

16 መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤ በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ።

17 የሚወድዱኝን እወድዳቸዋለሁ፤ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።

18 ሀብትና ክብር፣ ዘላቂ ብልጽግናና ስኬት በእኔ ዘንድ አሉ።

19 ፍሬዬ ከንጹሕ ወርቅ ይበልጣል፤ ስጦታዬም ከነጠረ ብር።

20 እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፤ በፍትሕም ጐዳና እጓዛለሁ፤

21 ለሚወድዱኝ ብልጽግና እሰጣለሁ፤ ግምጃ ቤታቸውንም እሞላለሁ።

22 “እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት፣ የተግባሮቹ መጀመሪያ አድርጎ አመጣኝ፤

23 ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣ ከጥንት ከዘላለም ተሾምሁ።

24 ከውቅያኖሶች በፊት፣ የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት ተወለድሁ፤

25 ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኰረብቶችም በፊት ተወለድሁ፤

26 ምድርን ወይም ሜዳዎቿን፣ ወይም ምንም ዐይነት የዓለም ትቢያን ከመፍጠሩ በፊት እኔ ተወለድሁ።

27 ሰማያትን በዘረጋ ጊዜ፣ በውቅያኖስ ላይ የአድማስ ምልክት ባደረገ ጊዜ እኔ እዚያ ነበርሁ፤

28 ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፣ የውቅያኖስን ምንጮች በመሠረተ ጊዜ፣

29 ለባሕር ድንበርን በከለለ ጊዜ፣ ውሆችም የርሱን ትእዛዝ እንዳያልፉ፣ የምድርንም መሠረቶች ወሰን ባበጀ ጊዜ፣

30 በዚያ ጊዜ ከጐኑ ዋና ባለሙያ ነበርሁ። ሁልጊዜ በፊቱ ሐሤት እያደረግሁ፣ ዕለት ተዕለት በደስታ እሞላ ነበር፤

31 የርሱ በሆነው መላው ዓለም ሐሤት እያደረግሁ፣ በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር።

32 “እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ መንገዴን የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው።

33 ምክሬን አድምጡ፤ ጥበበኞች ሁኑ፤ ቸልም አትበሉት።

34 ብፁዕ ነው፤ በየዕለቱ ደጃፌ ላይ የሚጠብቅ፣ በበራፌ ላይ የሚጠባበቅ፣ የሚያዳምጠኝ ሰው፤

35 የሚያገኘኝ ሁሉ ሕይወትን ያገኛልና፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል።

36 የሚያጣኝ ሁሉ ግን ራሱ ይጐዳል፤ የሚጠሉኝም ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告