Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ምሳሌ 29 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ከብዙ ተግሣጽ በኋላ ዐንገቱን የሚያደነድን ሰው፣ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።

2 ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል።

3 ጥበብን የሚወድድ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤ የአመንዝራዎች ወዳጅ ግን ሀብቱን ያባክናል።

4 ፍትሕን በማስፈን ንጉሥ አገርን ያረጋጋል፤ ጕቦ ለማግኘት የሚጐመጅ ግን ያፈራርሳታል።

5 ባልንጀራውን የሚሸነግል፣ ለገዛ እግሩ መረብ ይዘረጋል።

6 ክፉ ሰው በራሱ ኀጢአት ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ይዘምራል፤ ደስም ይለዋል።

7 ጻድቅ ስለ ድኾች ፍትሕ ያውቃል፤ ክፉ ግን ደንታ የለውም።

8 ተሳዳቢዎች ከተማን ያውካሉ፤ ጠቢባን ግን ቍጣን ያበርዳሉ።

9 ጠቢብ ሰው ከቂል ጋራ ወደ ሸንጎ ቢሄድ፣ ቂሉ ይቈጣል፤ ያፌዛል፤ ሰላምም አይኖርም።

10 ደም የተጠሙ ሰዎች ሐቀኛን ሰው ይጠላሉ፤ ቅን የሆነውንም ለመግደል ይሻሉ።

11 ሞኝ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቅቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል።

12 ገዥ የሐሰት ወሬ የሚሰማ ከሆነ፣ ሹማምቱ ሁሉ ክፉዎች ይሆናሉ።

13 ድኻውና ጨቋኙ የጋራ ነገር አላቸው፤ እግዚአብሔር ለሁለቱም የዐይን ብርሃንን ሰጥቷቸዋል።

14 ንጉሥ ለድኻ ትክክለኛ ፍርድ ቢሰጥ፣ ዙፋኑ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

15 የተግሣጽ በትር ጥበብን ታጐናጽፋለች፤ መረን የተለቀቀ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል።

16 ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ኀጢአት ይበዛል፤ ጻድቃን ግን የእነርሱን ውድቀት ያያሉ።

17 ልጅህን ቅጣው፤ ሰላም ይሰጥሃል፤ ነፍስህንም ደስ ያሰኛታል።

18 ራእይ በሌለበት ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተባረከ ነው።

19 አገልጋይ በቃል ብቻ ሊታረም አይችልም፤ ቢያስተውለውም እንኳ በጀ አይልም።

20 በችኰላ የሚናገርን ሰው ታያለህን? ከርሱ ይልቅ ሞኝ ተስፋ አለው።

21 ሰው አገልጋዩን ከልጅነቱ ጀምሮ ቢያቀማጥል፣ የኋላ ኋላ ሐዘን ያገኘዋል።

22 ቍጡ ሰው ጠብን ይጭራል፤ ግልፍተኛም ብዙ ኀጢአት ይሠራል።

23 ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብርን ይጐናጸፋል።

24 የሌባ ግብረ አበር የገዛ ራሱ ጠላት ነው፤ የመሐላውን ርግማን እየሰማ ጭጭ ይላል።

25 ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል።

26 ብዙዎች በገዥ ፊት ተደማጭነት ማግኘት ይሻሉ፤ ሰው ፍትሕ የሚያገኘው ግን ከከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

27 ጻድቃን አታላዮችን ይጸየፋሉ፤ ክፉዎችም ቅኖችን ይጠላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告