Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ምሳሌ 26 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 በረዶ በበጋ፣ ዝናብ በመከር እንደማያስፈልግ ሁሉ፣ ክብርም ለሞኝ አይገባውም።

2 ክንፎቿን እንደምታርገበግብ ድንቢጥ ወይም ቱር እንደምትል ጨረባ፣ ከንቱ ርግማንም በማንም ላይ አይደርስም።

3 ለፈረስ ዐለንጋ፣ ለአህያ መሸበቢያ፣ ለሞኝ ጀርባም በትር ይገባዋል።

4 ሞኝን እንደ ቂልነቱ አትመልስለት፤ አለዚያ አንተም ራስህ እንደ እርሱ ትሆናለህ።

5 ሞኝን እንደ ቂልነቱ መልስለት፤ አለዚያ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል።

6 በሞኝ እጅ መልእክትን መላክ፣ የገዛ እግርን እንደ መቍረጥ ወይም መርዝ እንደ መጋት ነው።

7 በሞኝ አንደበት የሚነገር ምሳሌ፣ የሰለለ የሽባ ሰው እግር ነው።

8 ለሞኝ ክብር መስጠት፣ በወንጭፍ ላይ ድንጋይ እንደ ማሰር ነው።

9 በሞኞች አንደበት የሚነገር ምሳሌ፣ በሰካራም እጅ እንዳለ እሾኽ ነው።

10 ሞኝን ወይም የትኛውንም ዐላፊ አግዳሚ የሚቀጥር፣ ፍላጻውን በነሲብ እየወረወረ ወገኖቹን እንደሚያቈስል ቀስተኛ ነው።

11 ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ሁሉ፣ ሞኝም ቂልነቱን ይደጋግማል።

12 ራሱን እንደ ጠቢብ የሚቈጥረውን ሰው አይተሃልን? ከርሱ ይልቅ ለሞኝ ተስፋ አለው።

13 ሰነፍ፣ “በመንገድ ላይ አንበሳ አለ፤ አስፈሪ አንበሳ በጐዳና ላይ ይጐማለላል” ይላል።

14 መዝጊያ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፣ ሰነፍም በዐልጋው ላይ ይገላበጣል።

15 ሰነፍ እጁን ወጭት ውስጥ ያጠልቃል፤ ወደ አፉ ለመመለስ ግን እጅግ ይታክታል።

16 በማስተዋል መልስ ከሚሰጡ ከሰባት ሰዎች ይልቅ፣ ሰነፍ ራሱን ጠቢብ አድርጎ ይቈጥራል።

17 በሌሎች ጠብ ጥልቅ የሚል መንገደኛ፣ የውሻ ጆሮ እንደሚይዝ ሰው ነው።

18 ትንታግ ወይም የሚገድል ፍላጻ እንደሚወረውር እብድ፣

19 “ቀልዴን እኮ ነው” እያለ ባልንጀራውን የሚያታልል ሰውም እንደዚሁ ነው።

20 ዕንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ አሾክሻኪ ከሌለም ጠብ ይበርዳል።

21 ከሰል ፍምን፣ ዕንጨትም እሳትን እንደሚያቀጣጥል፣ አዋኪ ሰውም ጠብን ያባብሳል።

22 የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤ ወደ ሰው ውስጠኛው ክፍል ዘልቆ ይገባል።

23 ክፋትን በልብ ቋጥሮ ለስላሳ ቃል የሚናገር ከንፈር፣ በብር ፈሳሽ እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቃ ነው።

24 ተንኰለኛ በከንፈሩ ይሸነግላል፤ በልቡ ግን ክፋትን ይቋጥራል።

25 ንግግሩ ማራኪ ቢሆንም አትመነው፤ ሰባት ርኩሰት ልቡን ሞልቶታልና።

26 ተንኰሉ በሽንገላው ይሸፈን ይሆናል፤ ነገር ግን ክፋቱ በጉባኤ ይገለጣል።

27 ጕድጓድ የሚምስ ራሱ ይገባበታል፤ ድንጋይ የሚያንከባልልም ተመልሶ በላዩ ላይ ይገለበጥበታል።

28 ሐሰተኛ ምላስ የጐዳቻቸውን ትጠላለች፤ ሸንጋይ አንደበትም ጥፋትን ታመጣለች።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告