Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ምሳሌ 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።

2 የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤ የሚያስቈጣውም ሰው ሕይወቱን ለመከራ ይዳርጋል።

3 ከጠብ መራቅ ለሰው ክብሩ ነው፤ ቂል ሁሉ ግን ለጥል ይቸኵላል።

4 ሰነፍ ሰው በወቅቱ አያርስም፤ ስለዚህ በመከር ወራት ይፈልጋል፤ አንዳችም አያገኝም።

5 የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል።

6 ብዙ ሰው ጽኑ ፍቅር እንዳለው ይናገራል፤ ታማኝን ሰው ግን ማን ሊያገኘው ይችላል?

7 ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል፤ ከርሱም በኋላ የሚከተሉት ልጆቹ ብፁዓን ናቸው።

8 ንጉሥ ለፍርድ ዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ ክፉውን ሁሉ በዐይኖቹ አበጥሮ ይለያል።

9 ለመሆኑ፣ “ልቤን በንጽሕና ጠብቄአለሁ፤ ንጹሕ ነኝ፤ ኀጢአት የለብኝም” የሚል ማን ነው?

10 ሁለት ዐይነት ሚዛን፣ ሁለት ዐይነት መስፈሪያ፣ ሁለቱንም እግዚአብሔር ይጸየፋቸዋል።

11 ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል።

12 የሚሰሙ ጆሮዎች፣ የሚያዩ ዐይኖች፣ ሁለቱንም እግዚአብሔር ሠርቷቸዋል።

13 እንቅልፍ አትውደድ፤ አለዚያ ድኻ ትሆናለህ፤ ዐይንህን ክፈት፤ የተትረፈረፈ ምግብ ይኖርሃል።

14 ዕቃ የሚገዛ፣ “የማይረባ ነው፤ የማይረባ ነው” ብሎ ያራክሳል፤ ሲመለስ ግን በግዥው ይኵራራል።

15 ወርቁም አለ፤ ቀዩም ዕንቍ ተትረፍርፏል፤ ዕውቀት የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ብርቅ ጌጦች ናቸው።

16 ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሆነውን ልብሱን ግፈፈው፤ ለባዕድ ሴት የተዋሰውን በቃሉ ዐግተው።

17 ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ይጣፍጠዋል፤ በመጨረሻ ግን አፉን ኰረት ሞልቶት ያገኘዋል።

18 ምክር ጠይቀህ ዕቅድ አውጣ፤ ጦርነት የምትገጥም ከሆነ መመሪያ ተቀበል።

19 ሐሜተኛ ምስጢር ያባክናል፤ ስለዚህ ለፍላፊን ሰው አርቀው።

20 አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፣ መብራቱ በድቅድቅ ጨለማ ይጠፋል።

21 ከጅምሩ ወዲያው የተገኘ ርስት፣ በመጨረሻ በረከት አይኖረውም።

22 “ለደረሰብኝ በደል ብድሬን ባልመልስ!” አትበል፤ እግዚአብሔርን ጠብቅ፤ እርሱ ይታደግሃል።

23 ሁለት ዐይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ አባይ ሚዛን አይወደድም።

24 የሰው አካሄዱ በእግዚአብሔር ይመራል፤ ሰውስ የገዛ መንገዱን እንዴት ማስተዋል ይችላል?

25 በችኰላ ስእለት መሳል፣ ከተሳሉም በኋላ ማቅማማት ለሰው ወጥመድ ነው።

26 ጠቢብ ንጉሥ ክፉዎችን አበጥሮ ይለያል፤ የመውቂያ መንኰራኵርንም በላያቸው ላይ ይነዳል።

27 የሰው መንፈስ ለእግዚአብሔር መብራት ነው፤ ውስጣዊ ማንነቱንም ይፈትሻል።

28 ፍቅርና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ በፍቅርም ዙፋኑ ይጸናል።

29 የጕልማሶች ክብር ብርታታቸው፣ የሽማግሌዎችም ሞገስ ሽበታቸው ነው።

30 የሚያቈስል በትር ክፋትን ያስወግዳል፤ ግርፋትም የውስጥ ሰውነትን ያጠራል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告