Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ምሳሌ 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ጠብ እያለ ግብዣ ከሞላበት ቤት ይልቅ፣ በሰላምና በጸጥታ ድርቆሽ ይሻላል።

2 ጠቢብ አገልጋይ በወራዳ ልጅ ላይ ሥልጣን ይኖረዋል፤ ከወንድማማቾቹም እንደ አንዱ ውርስ ይካፈላል።

3 ብር በማቅለጫ፣ ወርቅም በከውር፤ እግዚአብሔርም ልብን ይፈትናል።

4 እኩይ ሰው ክፉ ንግግር ያዳምጣል፤ ሐሰተኛም የተንኰለኛን አንደበት በጥንቃቄ ይሰማል።

5 በድኾች የሚያፌዝ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤ በሌላው ሰው መከራ ደስ የሚለው ከቅጣት አያመልጥም።

6 የልጅ ልጆች ለአረጋውያን ዘውድ ናቸው፤ ወላጆችም ለልጆቻቸው አለኝታ ናቸው።

7 መልካም አነጋገር ለሞኝ አይሰምርለትም፤ ለገዥ ሐሰተኛ አንደበት የቱን ያህል የከፋ ይሆን!

8 እጅ መንሻ ለሰጪው እንደ ድግምት ዕቃ ነው፤ በሄደበትም ቦታ ሁሉ ይሳካለታል።

9 በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ያዳብራል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የልብ ወዳጆችን ይለያያል።

10 መቶ ግርፋት ሞኝን ከሚሰማው ይልቅ፣ ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል።

11 ክፉ ሰው ዐመፅን ብቻ ይፈልጋል፤ በርሱም ላይ ጨካኝ መልእክተኛ ይላክበታል።

12 ሞኝን በቂልነቱ ከመገናኘት፣ ግልገሎቿን የተነጠቀችን ድብ መጋፈጥ ይሻላል።

13 በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልስ ሰው፣ ክፉ ነገር ከቤቱ አይርቅም።

14 ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ።

15 በደለኛውን ማጽደቅ ሆነ፣ ጻድቁን በደለኛ ማድረግ፣ ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸው።

16 ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣ ሞኝ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው?

17 ወዳጅ ምን ጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።

18 ልበ ቢስ ሰው ሰው ቃል በመግባት እጅ ይመታል፤ ለወዳጁም ዋስ ይሆናል።

19 ጠብ የሚወድድ ኀጢአትን ይወድዳል፤ በሩን ከፍ አድርጎ የሚሠራም ጥፋትን ይጋብዛል።

20 ጠማማ ልብ ያለው ሰው አይሳካለትም፤ በአንደበቱ የሚቀላምድም መከራ ላይ ይወድቃል።

21 ሞኝ ልጅ መውለድ ሐዘን ያስከትላል፤ የተላላም አባት ደስታ የለውም።

22 ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል።

23 ክፉ ሰው ፍትሕ ለማዛባት፣ በስውር ጕቦ ይቀበላል።

24 አስተዋይ ሰው ጥበብን ከፊቱ አይለያትም፤ የሞኝ ዐይኖች ግን እስከ ምድር ዳርቻ ይንከራተታሉ።

25 ሞኝ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤ ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል።

26 ንጹሑን ሰው መቅጣት ተገቢ አይደለም፤ ሹሞችን ስለ ቅንነታቸው መግረፍ መልካም አይደለም።

27 ዐዋቂ ሰው ንግግሩ ቍጥብ ነው፤ አስተዋይም መንፈሱ የረጋ ነው።

28 ቂል እንኳ ዝም ቢል ጠቢብ፣ አንደበቱንም ቢገዛ አስተዋይ ይመስላል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告