ምሳሌ 12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ መታረምን የሚጠላ ግን ደነዝ ነው። 2 መልካም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ግን እግዚአብሔር ይፈርድበታል። 3 ሰው በክፋት ላይ ተመሥርቶ ሊጸና አይችልም፤ ጻድቃን ግን ከቦታቸው አይነቃነቁም። 4 መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሚስት ግን ዐጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት። 5 የጻድቃን ሐሳብ ቀና ነው፤ የክፉዎች ምክር ግን ሸር አለበት። 6 የክፉዎች ቃል ደም ለማፍሰስ ታደባለች፤ የቅኖች ንግግር ግን ይታደጋቸዋል። 7 ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፤ ድራሻቸውም ይጠፋል፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። 8 ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ ጠማማ ልብ ያላቸው ግን የተናቁ ናቸው። 9 የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል። 10 ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤ ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው። 11 መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ልበ ቢስ ነው። 12 ኃጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤ የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል። 13 ክፉ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፤ ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል። 14 ሰው ከከንፈሩ ፍሬ የተነሣ በበጎ ነገር ይሞላል፤ እንደ እጁ ሥራም ተገቢውን ዋጋ ያገኛል። 15 ቂል ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል። 16 ቂል ሰው ቍጣው ወዲያውኑ ይታወቅበታል፤ አስተዋይ ሰው ግን ስድብን ንቆ ይተዋል። 17 ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል። 18 ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል። 19 እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው። 20 ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤ ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው። 21 ጻድቃን ጕዳት አያገኛቸውም፤ ክፉዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው። 22 እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከንፈርን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ደስ ይለዋል። 23 አስተዋይ ሰው ዕውቀቱን ይሰውራል፤ የሞኞች ልብ ግን ቂልነትን ይነዛል። 24 ትጉህ እጆች ለገዥነት ሲያበቁ፣ የስንፍና ፍጻሜ ግን የባርነት ሥራ ነው። 25 ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሠኘዋል። 26 ጻድቅ ሰው ለወዳጁ መልካም ምክር ይሰጣል፤ የክፉዎች መንገድ ግን ወደ ስሕተት ይመራቸዋል። 27 ሰነፍ ዐድኖ ያመጣውን እንኳ አይጠብስም፤ ትጉህ ሰው ግን ለንብረቱ ዋጋ ይሰጣል። 28 በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ፤ በዚያ ጐዳና ላይ ሞት የለም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.