Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ነህምያ 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በቅጥሩ ሥራ ላይ የተነሣ ሌላ ታቃውሞ

1 እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለበሮቹ መዝጊያ ባልገጥምላቸውም እንኳ፣ ቅጥሩን መሥራቴንና የቀረ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረባዊው ጌሳምና የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣

2 ሰንባላጥና ጌሳም፣ “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንገናኝ” ሲሉ ይህችን መልእክት ላኩብኝ። እነርሱ ግን እኔን ለመጕዳት ዐቅደው ነበር።

3 እኔም፣ “ታላቅ ሥራ እየሠራሁ ስለ ሆነ፣ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት ይህን መልስ የሚያደርሱ መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላክሁ።

4 አራት ጊዜም ይህንኑ ዐይነት መልእክት ላኩብኝ፤ እኔም በእያንዳንዱ ጊዜ ያንኑ መልስ ሰጠሁ።

5 ከዚያም ሰንባላጥ ለዐምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤

6 የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤ “አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቷል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣

7 ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።”

8 እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት።

9 ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።

10 አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሄጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ።

11 እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ።

12 በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦቢያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ።

13 በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው።

14 አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦቢያንና ሰንባላጥን ዐስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም ዐስብ።


የቅጥሩ ሥራ መጠናቀቅ

15 ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ ዐምስተኛ ቀን፣ በዐምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ።

16 ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን ሲሰሙ፣ በዙሪያችን ያሉ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፤ በራሳቸው መተማመንም አልቻሉም፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን ርዳታ መሆኑን ተገንዝበዋል።

17 በዚያ ጊዜ የይሁዳ መኳንንት ለጦቢያ ብዙ ደብዳቤ ይልኩ ነበር፤ ከጦቢያም መልስ ይላክላቸው ነበር።

18 በይሁዳ የሚኖሩ ሰዎች ምለውለት ነበር፤ ምክንያቱም የኤራ ልጅ የሴኬንያ ዐማት ከመሆኑም በላይ ልጁ ዮሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር።

19 ከዚህም በተጨማሪ ስለ መልካም ሥራው በየጊዜው ይነግሩኝና እኔም ያልሁትን ይነግሩት ነበር፤ ጦቢያም እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤ ይልክብኝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告