ነህምያ 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምአዲሶቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች 11፥3-19 ተጓ ምብ – 1ዜና 9፥1-17 1 በዚህ ጊዜ የሕዝቡ መሪዎች መኖሪያቸውን በኢየሩሳሌም አደረጉ፤ ከቀረው ሕዝብ ከዐሥር አንዱ እጅ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም፣ የቀሩት ዘጠኙ እጅ ደግሞ በየራሳቸው ከተሞች እንዲኖሩ ዕጣ ተጣጣሉ። 2 ሕዝቡም በኢየሩሳሌም ለመኖር በራሳቸው ፈቃድ የተነሣሡትን ሰዎች ሁሉ አመሰገኑ። 3 እንግዲህ በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የአውራጃዪቱ መሪዎች እነዚህ ናቸው፤ በዚህ ጊዜም በይሁዳ ከተሞች የሚኖሩ የተወሰኑ እስራኤላውያን፣ ካህናት፣ ሌዋውያን፣ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና የሰሎሞን አገልጋዮች ዘሮች እያንዳንዳቸው በተለያዩ ከተሞች ባለ በየራሳቸው ንብረት ላይ ተቀመጡ፤ 4 ከይሁዳና ከብንያም ወገን የሆኑት የተቀሩት ሰዎች ደግሞ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፤ ከይሁዳ ዘሮች፦ ከፋሬስ ዘር የመላልኤል ልጅ፣ የሰፋጥያስ ልጅ፣ የአማርያ ልጅ፣ የዘካርያስ ልጅ፣ የዖዝያ ልጅ አታያ፤ 5 ከሴሎ ዘር የዘካርያስ ልጅ፣ የዮያሪብ ልጅ፣ የዓዳያ ልጅ፣ የፆዛያ ልጅ፣ የኮልሖዜ ልጅ፣ የባሮክ ልጅ መዕሤያ። 6 በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የፋሬስ ዘሮች በጠቅላላ 468 ብርቱ ሰዎች ናቸው። 7 ከብንያም ዘሮች፦ የየሻያ ልጅ፣ የኢቲኤል ልጅ፣ የመዕሤያ ልጅ፣ የቆላያ ልጅ፣ የፈዳያ ልጅ፣ የዮእድ ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ ሰሉ፤ 8 ተከታዮቹም ጌቤና ሳላይ 928 ወንዶች፤ 9 የእነዚህም አለቃ የዝክሪ ልጅ ኢዮኤል ሲሆን፣ የሐስኑአ ልጅ ይሁዳ የከተማዪቱ ሁለተኛ አውራጃ የበላይ ነበር። 10 ከካህናቱ፦ የዮያሪብ ልጅ ዮዳኤ፤ ያኪን፤ 11 የእግዚአብሔር ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ፣ የኬልቅያስ ልጅ ሠራያ፤ 12 የቤተ መቅደሱን ሥራ ያከናወኑት ወንድሞቻቸው፣ 822 ሰዎች፤ የመልክያ ልጅ፣ የፋስኮር ልጅ፣ የዘካርያስ ልጅ፣ የአማሲ ልጅ፣ የፈላልያ ልጅ፣ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ፤ 13 ወንድሞቹ የሆኑት የየቤተ ሰቡ አለቆች 242 ወንዶች፤ የኢሜር ልጅ የምሺሌሞት ልጅ፣ የአሕዛይ ልጅ፣ የኤዝርኤል ልጅ አማስያ፤ 14 እንዲሁም ብርቱ የሆኑት ወንድሞቹ 128 ሰዎች፤ የእነርሱም ዋና አለቃ የሐግዶሊም ልጅ ዘብድኤል ነበር። 15 ከሌዋውያኑ፦ የቡኒ ልጅ፣ የአሳብያ ልጅ፣ የዓዝሪቃም ልጅ፣ የአሱብ ልጅ ሸማያ፤ 16 እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት የውጩ ሥራ ኀላፊዎች የነበሩት፣ ከሌዋውያን አለቆች ሁለቱ ሳባታይና ዮዛባት። 17 በምስጋናና በጸሎት ጊዜ ይመራ የነበረው የዋናው አለቃ የአሳፍ ልጅ፣ የዘብዲ ልጅ፣ የሚካ ልጅ መታንያ፣ ከወንድሞቹ ሁለተኛ የሆነው በቅቡቅያ፣ የኤዶታም ልጅ፣ የጋላል ልጅ፣ የሳሙስ ልጅ አብድያ። 18 በቅድስቲቱ ከተማ ውስጥ የነበሩት የሌዋውያኑ ቍጥር 284 ነበረ። 19 በር ጠባቂዎች፦ ዓቁብ፣ ጤልሞንና በሮቹን የሚጠብቁ ወንድሞቻቸው፣ 172 ሰዎች። 20 የቀሩት እስራኤላውያንም ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋራ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በየርስታቸው ተቀመጡ። 21 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች በዖፌል ኰረብታ ላይ ተቀመጡ፤ ሲሐና ጊሽጳ በእነርሱ ላይ ያዝዙ ነበር። 22 በኢየሩሳሌም የሌዋውያኑ ዋና አለቃ የሚካ ልጅ፣ የመታንያ ልጅ፣ የሐሸብያ ልጅ፣ የባኒ ልጅ ኦዚ ነበረ፤ ኦዚ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ለሚዘመረው መዝሙር ኀላፊ ከነበሩት ከአሳፍ ዘሮች አንዱ ነበረ። 23 መዘምራኑ የየዕለቱን ተግባራቸውን በሚቈጣጠረው በንጉሡ ትእዛዝ ሥር ነበሩ። 24 የይሁዳ ልጅ የዛራ ዘር የሆነው የሜሴዜቤል ልጅ ፈታያ ሕዝቡን በሚመለከት ጕዳይ ሁሉ የንጉሡ ተወካይ ነበር። 25 ከይሁዳ ሕዝብ ጥቂቱ በመንደሮችና በዕርሻ ቦታዎች፣ በቂርያት አርባቅና በዙሪያዋ ባሉ መኖሪያዎቿ፣ በዲቦንና በመኖሪያዎቿ፣ በይቀብጽኤልና በመንደሮቿ ተቀመጡ፤ 26 በኢያሱ፣ በሞላዳ፣ በቤትጳሌጥ፣ 27 በሐጻርሹዓል፣ በቤርሳቤህና በመኖሪያዎቿ፣ 28 በጺቅላግ፣ በምኮናና በመኖሪያዎቿ፣ 29 በዓይንሪሞን፣ በጾርዓ፣ በያርሙት፣ 30 በዛኖዋ፣ በዓዶላምና በመንደሮቻቸው፣ በለኪሶና በዕርሻዎቿ፣ በዓዜቃና በመንደሮቿ። ስለዚህ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ሄኖም ሸለቆ ባለው ስፍራ ሁሉ ተቀመጡ። 31 ከጌባዕ የመጡት የብንያም ዘሮች በማክማስ፣ በጋያ፣ በቤቴልና በመኖሪያዎቿ፣ 32 በዓናቶት፣ በኖብና በሐናንያ፣ 33 በሐጾር፣ በራማና በጊቴም፣ 34 በሐዲድ፣ በስቦይምና በንበላት፣ 35 በሎድና በኦኖ፣ ደግሞም ጌሃርሻም በተባለው ስፍራ ተቀመጡ። 36 በይሁዳ ከነበሩት ሌዋውያን ከፊሎቹ በብንያም ምድር ተቀመጡ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.