Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ናሆም 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የነነዌ አወዳደቅ

1 ነነዌ ሆይ፤ አጥቂ መጥቶብሻል፤ ምሽግሽን ጠብቂ፤ መንገድሽን ሰልዪ፤ ወገብሽን ታጠቂ፤ ኀይልሽን ሁሉ አሰባስቢ።

2 አጥፊዎች ባድማ ቢያደርጓቸውም፣ የወይን ተክል ቦታቸውን ቢያጠፉባቸውም፣ እንደ እስራኤል ክብር ሁሉ፣ እግዚአብሔር የያዕቆብንም ክብር ይመልሳል።

3 የወታደሮቹ ጋሻ ቀይ ነው፤ ተዋጊዎቹ ቀይ ልብስ ለብሰዋል፤ ዝግጁ በሆኑበት ቀን፣ የሠረገሎቹ ብረት ያብረቀርቃል፤ የጦሩ ዘንግ ይወዛወዛል።

4 ሠረገሎች በአደባባይ ወዲያ ወዲህ ይከንፋሉ፤ በመንገዶችም ላይ ይርመሰመሳሉ፤ የሚንበለበል ፋና ይመስላሉ፤ እንደ መብረቅም ይወረወራሉ።

5 ምርጥ ተዋጊዎቹን ይጠራል፤ ዳሩ ግን መንገድ ላይ ይሰናከላሉ፤ ወደ ከተማዪቱ ቅጥር ይሮጣሉ፤ መከላከያ ጋሻውም በቦታው አለ።

6 የወንዙ በር ወለል ብሎ ተከፈተ፤ ቤተ መንግሥቱም ወደቀ።

7 ከተማዪቱ መማረኳና መወሰዷ እንደማይቀር፣ አስቀድሞ ተነግሯል፤ ሴቶች ባሪያዎቿ እንደ ርግብ ያለቅሳሉ፤ ደረታቸውንም ይደቃሉ።

8 ነነዌ እንደ ኵሬ ናት፤ ውሃዋም ይደርቃል፤ “ቁም! ቁም!” ብለው ይጮኻሉ፤ ነገር ግን ወደ ኋላ የሚመለስ የለም።

9 ብሩን ዝረፉ! ወርቁን ንጠቁ! በየግምጃ ቤቱ ያለው፣ የተከማቸውም ሀብት ስፍር ቍጥር የለውም።

10 ተበዝብዛለች፤ ተዘርፋለች፤ ተራቍታለች። ልብ ቀልጧል፤ ጕልበት ተብረክርኳል፤ ሰውነት ተንቀጥቅጧል፤ ፊት ሁሉ ገርጥቷል።

11 አሁን ታዲያ የአንበሶቹ ዋሻ፣ ደቦሎቻቸውን ያበሉበት ወንዱና ሴቷ አንበሳ የሄዱበት፣ ግልገሎችም ሳይፈሩ የተሰማሩበት ቦታ ወዴት ነው?

12 አንበሳው ለግልገሎቹ የሚበቃውን ያህል ገደለ፤ ለእንስቶቹም ዐንቆ ገደለላቸው፤ የገደለውን በማረፊያ ቦታው፣ የነጠቀውንም በዋሻው ሞልቶታል።

13 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በእናንተ ላይ ተነሥቼባችኋለሁ፤ ሠረገሎቻችሁን አቃጥዬ አጨሳለሁ፤ ደቦል አንበሶቻችሁን ሰይፍ ይበላል፤ የምትበሉትን በምድር ላይ አልተውላችሁም፤ የመልእክተኞቻችሁም ድምፅ፣ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告