Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሚክያስ 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የእስራኤል መከራ

1 ለእኔ ወዮልኝ! የወይን ዕርሻ በሚቃረምበት ጊዜ፣ የበጋ ፍራፍሬ እንደሚለቅም ሰው ሆኛለሁ፤ የሚበላ የወይን ዘለላ የለም፤ የምንጓጓለት፣ ቶሎ የሚደርሰው በለስም አልተገኘም።

2 የሚታመን ሰው ከምድር ጠፍቷል፤ አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፤ ሰው ሁሉ ደም ለማፍሰስ ያደባል፤ እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል።

3 እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ ገዥው እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ ፈራጁ ጕቦ ይቀበላል፤ ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ።

4 ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣ እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት ነው፤ የጠባቂዎቻችሁ ቀን ደርሷል፤ የአምላክ የፍርድ ቀን መጥቷል፤ የሚሸበሩበትም ጊዜ አሁን ደርሷል።

5 ባልንጀራህን አትመን፤ በጓደኛህም አትታመን፤ በዕቅፍህ ለምትተኛዋ እንኳ፣ ስለምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ።

6 ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፣ ምራት በዐማቷ ላይ ትነሣለች፤ የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ ናቸውና።

7 እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ የድነቴን አምላክ እጠብቃለሁ፤ አምላኬ ይሰማኛል።


እስራኤል ትነሣለች

8 ጠላቴ ሆይ፤ በእኔ ላይ በደረሰው ደስ አይበልሽ! ብወድቅም እንኳ እነሣለሁ፤ በጨለማ ብቀመጥ እንኳ፣ እግዚአብሔር ብርሃኔ ይሆናል።

9 እርሱን ስለ በደልሁ፣ እስኪቆምልኝ እስኪፈርድልኝም ድረስ፣ የእግዚአብሔርን ቍጣ እቀበላለሁ፤ እርሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል፤ እኔም ጽድቁን አያለሁ።

10 ጠላቴም ታያለች፤ ኀፍረትንም ትከናነባለች፤ “አምላክህ እግዚአብሔር የት አለ?” ያለችኝን፣ ዐይኖቼ ውድቀቷን ያያሉ፤ አሁንም እንኳ፣ እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች።

11 ቅጥሮቻችሁን የምትሠሩበት፣ ድንበራችሁንም የምታሰፉበት ቀን ይመጣል።

12 በዚያ ቀን ሰዎች፣ ከአሦር እስከ ግብጽ ከተሞች፣ ከግብጽ እስከ ኤፍራጥስ፣ ከባሕር ወደ ባሕር፣ ከተራራ ወደ ተራራ ወደ እናንተ ይመጣሉ።

13 ከሥራቸው የተነሣ፣ በነዋሪዎቿ ምክንያት ምድር ባድማ ትሆናለች።


ጸሎትና ውዳሴ

14 ብቻቸውን በዱር ውስጥ፣ በለመለመ መስክ የሚኖሩትን፣ የርስትህ መንጋ የሆኑትን፣ ሕዝብህን በበትርህ ጠብቅ፤ እንደ ቀድሞው ዘመን፣ በባሳንና በገለዓድ ይሰማሩ።

15 “ከግብጽ እንደ ወጣህበት ዘመን ሁሉ፣ ታምራቴን አሳያቸዋለሁ።”

16 አሕዛብ ያያሉ፣ ያፍራሉም፤ ኀይላቸውን ሁሉ ያጣሉ፤ አፋቸውን በእጃቸው ይይዛሉ፤ ጆሯቸውም ትደነቍራለች።

17 በደረታቸው እንደሚሳቡ ፍጥረታት፣ እንደ እባብም ትቢያ ይልሳሉ፤ ከዋሻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ፤ በፍርሀትም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እናንተንም ይፈራሉ።

18 የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።

19 ተመልሰህ ትራራልናለህ፤ ኀጢአታችንን በእግርህ ትረግጣለህ፤ በደላችንንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለህ።

20 ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል እንደ ገባህላቸው፣ ለያዕቆብ ታማኝነትን፣ ለአብርሃምም ምሕረትን ታደርጋለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告