Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሚክያስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የእግዚአብሔር ተራራ

1 በመጨረሻው ዘመን፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ፣ ከተራሮችም ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።

2 ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ በጐዳናውም እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።” ሕግ ከጽዮን፤ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።

3 እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤ በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤ ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።

4 እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሯልና።

5 አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክታቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።


የ እግዚአብሔር ዕቅድ

6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤ ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣ ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።

7 የሽባዎችን ትሩፍ፣ የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤ ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።

8 አንተ የመንጋው መጠበቂያ ማማ ሆይ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ዐምባ ሆይ፤ የቀድሞው ግዛትህ ይመለስልሃል፤ የመንግሥትም ሥልጣን ለኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ይሆናል።”

9 አሁንስ እንደዚህ የምትጮኺው ለምንድን ነው? ንጉሥ የለሽምን? ምጥ እንደ ያዛት ሴት የተጨነቅሽው፣ መካሪሽ ስለ ጠፋ ነውን?

10 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ተጨነቂ፤ አሁንስ ከከተማ ወጥተሽ፣ በሜዳ ላይ መስፈር አለብሽና፤ ወደ ባቢሎን ትሄጃለሽ፤ በዚያ ከጠላት እጅ ትድኛለሽ። እግዚአብሔር በዚያ፣ ከጠላቶችሽ ይታደግሻል።

11 አሁን ግን ብዙ አሕዛብ፣ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል፤ እነርሱም፣ “የረከሰች ትሁን፤ ዐይናችንም ጽዮንን መዘባበቻ አድርጎ ይያት” ይላሉ።

12 ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ አያውቁም፤ በዐውድማ ላይ እንደ ነዶ የሚሰበስባቸውን፣ የርሱን ዕቅድ አያስተውሉም።

13 “የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ተነሥተሽ አበራዪ፤ የብረት ቀንድ እሰጥሻለሁና፤ የናስ ሰኰና እሰጥሻለሁ፤ አሕዛብንም ታደቅቂአቸዋለሽ።” በግፍ ያግበሰበሱትን ትርፍ ለእግዚአብሔር፣ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትለዪአለሽ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告