Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሚክያስ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መሪዎችና ነቢያት ተገሠጹ

1 ከዚያም እኔ እንዲህ አልሁ፤ “እናንተ የያዕቆብ መሪዎች፤ እናንተ የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤ ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን?

2 መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤ የሕዝቤን ቈዳ ገፈፋችሁ፤ ሥጋቸውንም ከዐጥንቶቻቸው ለያችሁ፤

3 የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ፤ ቈዳቸውን ገፈፋችሁ፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፤ በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣ በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቈራረጣችኋቸው።”

4 እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤ ካደረጉት ክፋት የተነሣ፣ በዚያ ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።

5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣ ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤ ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣ ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።

6 ስለዚህ ሌሊቱ ያለ ራእይ፣ ጨለማውም ያለ ሟርት ይመጣባችኋል፤ በነቢያት ላይ ፀሓይ ትጠልቅባቸዋለች፤ ቀኑም ይጨልምባቸዋል።

7 ባለራእዮች ያፍራሉ፤ ጠንቋዮችም ይዋረዳሉ፤ ሁሉም ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤ ከእግዚአብሔር መልስ የለምና።”

8 እኔ ግን፣ ለያዕቆብ በደሉን፣ ለእስራኤልም ኀጢአቱን እነግር ዘንድ፣ ኀይልን በእግዚአብሔር መንፈስ፣ ፍትሕና ብርታትም ተሞልቻለሁ።

9 እናንተ የያዕቆብ ቤት መሪዎች፣ እናንተ የእስራኤል ቤት ገዦች፣ ፍትሕን የምትንቁ፣ ትክክለኛ የሆነውንም ነገር ሁሉ የምታጣምሙ፤ ስሙ፤

10 ጽዮንን ደም በማፍሰስ፣ ኢየሩሳሌምን በክፋት የምትገነቡ፤ ስሙ።

11 መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።

12 ስለዚህ በእናንተ ምክንያት፣ ጽዮን እንደ ዕርሻ ትታረሳለች፣ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ የቤተ መቅደሱም ኰረብታ ዳዋ የወረሰው ጕብታ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告