Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሚክያስ 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል፣ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፤

2 እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤ ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤ ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣ ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።


በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ

3 እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያ ስፍራው ይመጣል፤ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።

4 ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤ በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣ በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።

5 ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣ ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው። የያዕቆብ በደል ምንድን ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?

6 “ስለዚህ ሰማርያን የፍርስራሽ ክምር፣ ወይን የሚተከልባትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ አወርዳለሁ፤ መሠረቷንም ባዶ አደርጋለሁ።

7 ጣዖቶቿ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤ ምስሎቿን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ ገጸ በረከቷን በዝሙት ዐዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣ አሁንም ገጸ በረከቷ የዝሙት ዐዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።”


ልቅሶና ሐዘን

8 በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይም እላለሁ፤ ባዶ እግሬንና ዕርቃኔን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፤ እንደ ጕጕትም አቃስታለሁ።

9 ቍስሏ የማይሽር ነውና፤ ለይሁዳ ተርፏል፤ እስከ ሕዝቤ መግቢያ በር፣ እስከ ኢየሩሳሌም እንኳ ደርሷል።

10 በጋት አታውሩት፤ ከቶም አታልቅሱ፤ በቤትዓፍራ፣ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።

11 እናንተ በሻፊር የምትኖሩ፣ ዕርቃናችሁን ሆናችሁ በኀፍረት ዕለፉ፤ በጸዓናን የሚኖሩ ከዚያ አይወጡም፤ ቤትዔጼል በሐዘን ላይ ናት፤ ለእናንተም መጠጊያ ልትሆን አትችልም።

12 ከመከራው መገላገልን በመሻት፣ በማሮት የሚኖሩ በሥቃይ ይወራጫሉ፤ እስከ ኢየሩሳሌም በር ሳይቀር፣ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቷልና።

13 እናንተ በለኪሶ የምትኖሩ፣ ፈረሶችን ከሠረገላው ጋራ አያይዙ፤ ለጽዮን ሴት ልጅ፣ የኀጢአት መጀመሪያ እናንተ ነበራችሁ፤ የእስራኤል በደል በእናንተ ዘንድ ተገኝቷልና።

14 ስለዚህ እናንተ ለሞሬሼትጌት፣ ማጫ ትሰጣላችሁ፤ የአክዚብ ከተማ፣ ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ትሆናለች።

15 እናንተ በመሪሳ የምትኖሩ ድል አድራጊ አመጣባችኋለሁ፤ ያ የእስራኤል ክብር የሆነው ወደ ዓዶላም ይመጣል።

16 ደስ ለምትሠኙባቸው ልጆቻችሁ፣ በሐዘን ራሳችሁን ተላጩ፤ ራሳችሁን እንደ አሞራ ራስ ተመለጡት፤ ከእናንተ በምርኮ ይወሰዳሉና።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告