Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ማርቆስ 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ
11፥7-10 ተጓ ምብ – ዮሐ 12፥12-15

1 ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፤

2 “በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፣ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡት፤

3 ማንም፣ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤ እርሱም ወዲያውኑ መልሶ ይልከዋል’ በሉት።”

4 እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ መንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙ፤ ፈቱትም።

5 በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፣ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው።

6 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው።

7 ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሶቻቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት።

8 ብዙ ሰዎች ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ከሜዳ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።

9 የቀደሙትና የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሆሳዕና!” “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!”

10 “የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት!” “ሆሳዕና በአርያም!”

11 ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለ መሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ ወደ ቢታንያ ወጣ።


ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጸዳ
11፥15-18 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥12-16 ፤ ሉቃ 19፥45-47 ፤ ዮሐ 2፥13-16

12 በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ።

13 እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።

14 ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።

15 ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤

16 ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።

17 ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት!’” አላቸው።

18 የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።

19 በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።


የበለሷ ዛፍ ደረቀች
11፥20-24 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥19-22

20 በማግስቱም ጧት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።

21 ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች!” አለው።

22 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤

23 እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል።

24 ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ይሆንላችሁማል።

25 እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። [

26 ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”]


በኢየሱስ ሥልጣን ላይ ጥያቄ ተነሣ
11፥27-33 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥23-27 ፤ ሉቃ 20፥1-8

27 እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፣

28 “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት።

29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ።

30 የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ!”

31 እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው’ ብንል፣ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤

32 ‘ከሰው ነው’ ብንል …” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ እንደ ሆነ ይቈጥር ስለ ነበር ፈሩ።

33 ስለዚህ ለኢየሱስ፣ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告