ማርቆስ 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየባልና የሚስት ፍች 10፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥1-9 1 ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው። 2 አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “አንድ ባል ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። 3 እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው። 4 እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍችውን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉ። 5 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። 6 ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ‘ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።’ 7 ‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፤ 8 ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። 9 ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” 10 እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። 11 እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በርሷ ላይ ያመነዝራል። 12 እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው። ኢየሱስ ሕፃናትን ባረከ 10፥13-16 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥13-15 ፤ ሉቃ 18፥15-17 13 ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። 14 ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 15 እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” 16 ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው። ሀብታሙ ወጣት 10፥17-31 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥16-30 ፤ ሉቃ 18፥18-30 17 ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጕልበቱ ተንበርክኮ፣ “መልካም መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። 18 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር መልካም ማንም የለም፤ 19 ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አታታልል፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።” 20 ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። 21 ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። 22 ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ። 23 ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው!” አላቸው። 24 ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው! 25 ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀልለዋል።” 26 ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። 27 ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው። 28 ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል!” አለው። 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም ዕርሻን የተወ ሁሉ፣ 30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋራ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም። 31 ነገር ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።” ኢየሱስ ዳግም ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ 10፥32-34 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥17-19 ፤ ሉቃ 18፥31-33 32 ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ 33 እንዲህም አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ 34 ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።” የያዕቆብና የዮሐንስ ጥያቄ 10፥35-45 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥20-28 35 ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት። 36 እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 37 እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት። 38 ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው። 39 እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት። ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40 ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው። 41 ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ። 42 ኢየሱስም ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዦች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸውም በእነርሱ ላይ እንደሚሠለጥኑባቸው ታውቃላችሁ፤ 43 በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ 44 ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 45 የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷልና።” ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን ፈወሰ 10፥46-52 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥29-34 ፤ ሉቃ 18፥35-43 46 ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋራ ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 47 እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 48 ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ። 49 ኢየሱስም ቆም ብሎ፣ “ጥሩት” አላቸው። እነርሱም ዐይነ ስውሩን፣ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል!” አሉት። 50 እርሱም ልብሱን ጥሎ፣ ዘልሎ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ። 51 ኢየሱስም፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዐይነ ስውሩም፣ “መምህር ሆይ፤ ዳግም እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው። 52 ኢየሱስም፣ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.