ሚልክያስ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለካህናት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 1 “አሁንም ካህናት ሆይ፤ ይህ ማስጠንቀቂያ ለእናንተ የተሰጠ ነው፤ 2 ባትሰሙ፣ ልባችሁንም ስሜን ለማክበር ባታዘጋጁ፣ ርግማን እሰድድባችኋለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ መርገም እለውጠዋለሁ፤ ልታከብሩኝ ልባችሁን አላዘጋጃችሁምና ረግሜዋለሁ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 3 “ዘራችሁን እገሥጻለሁ፤ የመሥዋዕታችሁን ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተም ከርሱ ጋራ ትወገዳላችሁ፤ 4 ከሌዊ ጋራ የገባሁት ኪዳን ይጸና ዘንድ፣ ይህን ማስጠንቀቂያ የላክሁት እኔ መሆኔንም ታውቃላችሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5 “ከርሱ ጋራ የገባሁት ኪዳን የሕይወትና የሰላም ኪዳን ነበር፤ እነርሱንም ሰጠሁት፤ ይህም ክብርን አመጣ፤ እርሱም አከበረኝ፤ ስሜን በመፍራትም ጸና። 6 እውነተኛ ትምህርት በአፉ ነበር፤ ምንም ዐይነት የሐሰት ነገር በአንደበቱ አልተገኘም፤ ከእኔ ጋራ በሰላምና በቅንነት ተራመደ፤ ብዙዎችንም ከኀጢአት መለሰ። 7 “ካህኑ የሁሉ ገዥ፣ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ስለ ሆነ ከንፈሮቹ ዕውቀትን ሊጠብቁ፣ ሰዎችም ከአንደበቱ ትምህርትን ሊፈልጉ ይገባል፤ 8 እናንተ ግን ከመንገዱ ወጥታችኋል፤ በትምህርታችሁም ብዙዎች እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል፤ የሌዊንም ኪዳን አፍርሳችኋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 9 “ስለዚህ በመንገዴ ስላልሄዳችሁና በትምህርታችሁም አድልዎ ስላደረጋችሁ፣ በሰዎች ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አድርጌአችኋለሁ።” የይሁዳ አለመታመን 10 ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ እርስ በርሳችን ታማኝነት በማጕደል የአባቶቻችንን ኪዳን ለምን እናረክሳለን? 11 ይሁዳ አልታመነም፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሟል፤ ይሁዳ የባዕድ አምላክ ሴት ልጅ በማግባት እግዚአብሔር የሚወድደውን መቅደስ አርክሷል። 12 ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ቢሆን፣ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ቍርባን ቢያመጣም እንኳ፣ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ድንኳን ያስወግደው። 13 ሌላው የምታደርጉት ነገር ደግሞ፣ የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ ታጥለቀልቃላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቍርባናችሁን ስለማይመለከትና በደስታም ከእጃችሁ ስለማይቀበል ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻላችሁም። 14 እናንተም፣ “ለምን ይህ ሆነ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይህ የሆነው የትዳር ጓደኛህን፣ አጋርህንና የቃል ኪዳን ሚስትህን አታልለሃታልና፣ እግዚአብሔር በአንተና በወጣትነት ሚስትህ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምስክር ስለ ሆነ ነው። 15 እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? በሥጋም በመንፈስም የርሱ ናቸው። ለምን አንድ አደረጋቸው? ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ዘር ይፈልግ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋራ ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ። 16 “ፍችን እጠላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፤ “ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም ሰው እጠላለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ታማኝነታችሁም አይጓደል። የፍርድ ቀን 17 እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችሁታል። እናንተም፣ “ያታከትነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ? “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነው፤ እርሱም በክፉዎች ደስ ይለዋል” ወይም “የፍትሕ አምላክ ወዴት ነው?” በማለታችሁ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.