ዘሌዋውያን 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምካህናቱ አገልግሎታቸውን ጀመሩ 1 በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንንና ልጆቹን እንዲሁም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራቸው። 2 አሮንንም እንዲህ አለው፤ “የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ እንቦሳ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ አውራ በግ ወስደህ፣ በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ ሁለቱም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ። 3 እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፤ ‘ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት እንከን የሌለባቸውን የአንድ ዓመት እንቦሳና የአንድ ዓመት ጠቦት፣ 4 ለኅብረት መሥዋዕት አንድ በሬና አንድ አውራ በግ በዘይት ከተለወሰ የእህል ቍርባን ጋራ በእግዚአብሔር ፊት ለመሠዋት አቅርቡ፤ እግዚአብሔር ዛሬ ይገለጥላችኋልና።’ ” 5 እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 6 ሙሴም፣ “የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ፣ እንድታደርጉት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ይህ ነው” አለ። 7 ሙሴ አሮንን፣ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተስርይላቸውም” አለው። 8 አሮንም ወደ መሠዊያው መጥቶ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት የቀረበውን እንቦሳ ዐረደው። 9 ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ግርጌ አፈሰሰው። 10 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት የኀጢአት መሥዋዕቱን ሥብ፣ ኵላሊቶቹንና የጕበቱን ሽፋን በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ 11 ሥጋውንና ቍርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው። 12 ከዚህ በኋላ አሮን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዐረደ፤ ልጆቹ ደሙን አቀበሉት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 13 ልጆቹም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ብልት አንድ በአንድ፣ ጭንቅላቱን ሳይቀር አምጥተው ሰጡት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ዐጥቦ በመሠዊያው ላይ ካለው ከሚቃጠለው መሥዋዕት በላይ አቃጠለ። 15 አሮንም የሕዝቡን መሥዋዕት አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ ዐረደው፤ እንደ ፊተኛው ሁሉ ይህንም በኀጢአት መሥዋዕትነት ሠዋው። 16 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አምጥቶ በሥርዐቱ መሠረት አቀረበው። 17 የእህል ቍርባኑን አመጣ፤ ከላዩም ዕፍኝ ሙሉ ወስዶ ጧት ጧት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 18 አሮንም ስለ ሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት የቀረቡትን በሬውንና አውራ በጉን ዐረደ፤ ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 19 የበሬውንና የአውራ በጉን ሥብ፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፤ ኵላሊቶቹንና የጕበቱን ሽፋን፣ 20 በፍርምባዎቹ ላይ አስቀመጡ፤ አሮንም ሥቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21 አሮንም ፍርምባዎቹንና የቀኝ ወርቹንም ሙሴ ባዘዘው መሠረት፣ የመወዝወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዘው። 22 አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘርግቶ ባረካቸው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱን፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ወረደ። 23 ከዚህ በኋላ፣ ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ከዚያ ሲወጡም ሕዝቡን ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24 እሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ፣ በመሠዊያው ላይ የነበረውን በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ባዩ ጊዜ እልል አሉ፤ በግንባራቸውም ተደፉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.