Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘሌዋውያን 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በማጕደልና ባልንጀራውን በማጭበርበር ባይታመን፣ እግዚአብሔርንም ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣

3 ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ኀጢአት ቢሠራ፣

4 በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤

5 በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ ዐምስተኛ በመጨመር ለባለንብረቱ ንብረቱ ይመልስ።

6 ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤

7 በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለ ማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።”


የሚቃጠል መሥዋዕት

8 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

9 “አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድድ ይደር።

10 ካህኑም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ሱሪውን ካጠለቀ በኋላ፣ የበፍታ ቀሚሱን ይልበስ፤ እሳቱ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቱን ከበላው በኋላ የሚቀረውን ዐመድ አንሥቶ፣ በመሠዊያው አጠገብ ያፍስስ።

11 ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይቀይር፤ ዐመዱንም ተሸክሞ ከሰፈር ውጭ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ይውሰድ።

12 በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምን ጊዜም አይጥፋ። ካህኑ ጧት ጧት እሳቱ ላይ ማገዶ ይጨምር፤ በእሳቱ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያዘጋጅ፤ በዚህም ላይ የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ ያቃጥል።

13 በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምን ጊዜም አይጥፋ።


የእህል ቍርባን

14 “ ‘የእህል ቍርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቍርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርቡት።

15 ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው።

16 የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ ቂጣውን በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት።

17 ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቍርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው።

18 ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ”

19 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤

20 “አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ያቅርቡት።

21 በሚገባ በዘይት ተለውሶ በምጣድ ላይ ይጋገር፤ ከዚያም የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ አቅርብ።

22 በርሱ ቦታ ተቀብቶ ካህን የሚሆነው ልጁ ይህን ያዘጋጅ፤ ለእግዚአብሔር የተመደበ ድርሻ ነውና ፈጽሞ ይቃጠል።

23 ካህኑ የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል እንጂ አይበላ።”


የኀጢአት መሥዋዕት

24 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

25 “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱም መሥዋዕት እዚያው በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

26 መሥዋዕቱንም የሚያቀርበው ካህን ይብላው፤ ይህም በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ በአደባባዩ ላይ ይበላ።

27 ሥጋውን የሚነካ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ ደሙ በልብስ ላይ ቢረጭ፣ ያን ልብስ በተቀደሰ ስፍራ ዕጠብ።

28 ሥጋው የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ የናስ ዕቃ ከሆነ ግን ተፈግፍጎ በውሃ ይታጠብ።

29 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

30 ነገር ግን ደሙ ማስተስረያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ ቅድስት የቀረበው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ በእሳት ይቃጠል እንጂ አይበላ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告