ዘሌዋውያን 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “ ‘አንድ ሰው ስላየውና ስለሚያውቀው ነገር ሕጋዊ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆን፣ ይህ ሰው ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል። 2 “ ‘ማንኛውም ሰው ሳያውቅ በሥርዐቱ መሠረት የተከለከለውን ርኩስ ነገር ቢነካ፣ ይኸውም፦ የረከሰ የአውሬ በድን ወይም የረከሰ የቤት እንስሳ በድን ወይም በደረቱ እየተሳበ የሚንቀሳቀሰውን የረከሰ ፍጥረት በድን ቢነካ ይህ ሰው ረክሷል፤ በደለኛም ነው። 3 ወይም የሰውን ርኩሰት ይኸውም ርኩስ የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ሳያውቅ ቢነካ፣ ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል። 4 ሰዎች በሚምሉበት በማናቸውም ነገር፣ በጎ ወይም ክፉ ለማድረግ ሳያስብ በግዴለሽነት ቢምል በኋላ ግን ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል። 5 ማንኛውም ሰው ከእነዚህ በአንዱ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ፣ የትኛውን ኀጢአት እንደ ሠራ ገልጾ መናዘዝ አለበት፤ 6 ስለ ኀጢአቱም ቅጣት የኀጢአት መሥዋዕት እንድትሆነው ከመንጋው አንዲት የበግ ወይም የፍየል እንስት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ካህኑም ስለ ኀጢአቱ ያስተሰርይለታል። 7 “ ‘ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች የመጀመሪያውን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 8 ወደ ካህኑም ያምጣቸው፤ እርሱም ለኀጢአት መሥዋዕት የምትሆነውን አስቀድሞ ያቅርብ፤ ራሷን ዐንገቷ ላይ ይቈልምም፤ ነገር ግን ቈርጦ አይጣል፤ 9 ከኀጢአት መሥዋዕቱም ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ላይ ይርጨው፤ የተረፈውም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ይፍሰስ፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 10 ካህኑም ቀደም ሲል በታዘዘው መሠረት ሁለተኛዋን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ ካህኑም የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 11 “ ‘ሰውየው ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ነገር ግን የኀጢአት መሥዋዕት ስለ ሆነ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤ 12 ከዚያም ለካህኑ ያቅርብ፤ ካህኑም ለመታሰቢያ እንዲሆን ዕፍኝ ሙሉ ይዝገንለት፤ በእሳት ከሚቀርበውም ቍርባን በላይ አድርጎ ለእግዚአብሔር በመሠዊያው ላይ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 13 ሰውየው ከእነዚህ በአንዱ ኀጢአት ቢሠራ፣ ካህኑ በዚህ ሁኔታ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። ከመሥዋዕቱ የተረፈውም እንደ እህል ቍርባን ሁሉ ለካህኑ ይሆናል።’ ” የበደል መሥዋዕት 14 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 15 “ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ባይታመን፤ ከተቀደሰ ከማናቸውም ነገር በማጕደል ኀጢአት ቢሠራ፣ ከመንጋው እንከን የሌለበትን አውራ በግ የበደል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። የዋጋውም ግምት በቤተ መቅደሱ ሰቅል መሠረት ተመዝኖ በጥሬ ብር ይሁን፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። 16 ከተቀደሱ ነገሮች ያጐደለውንም ይተካ፤ የዚህንም ተመን አንድ ዐምስተኛ በላዩ ጨምሮ ለካህኑ ይስጥ፤ ካህኑም ከበጉ ጋራ የበደል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 17 “ማንኛውም ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች ሳያውቅ አንዱን ተላልፎ ቢገኝ በደለኛ ነው፤ በኀጢአቱም ይጠየቅበታል። 18 እርሱም ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት የሚሆን እንከን የሌለበት አውራ በግ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ዋጋውም ተመጣጣኝ ይሁን። ካህኑም በዚህ ሁኔታ ሰውየው ሳያውቅ ስለ ፈጸመው ስሕተት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 19 ይህ የበደል መሥዋዕት ነው። ሰውየውም በእግዚአብሔር ፊት ጥፋት በመፈጸሙ በደለኛ ነው።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.