ዘሌዋውያን 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምስለ ስጦታ የወጣ ሕግ 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ማንኛውም ሰው ተመጣጣኙን ዋጋ በመክፈል ለእግዚአብሔር ሰውን ለመስጠት የተለየ ስእለት ቢሳል፣ 3 ዕድሜው ከሃያ እስከ ስድሳ ዓመት ለሆነ ወንድ፣ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት፣ ግምቱ ዐምሳ ጥሬ ሰቅል ብር ይሁን። 4 ለሴት ከሆነ ግምቱ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። 5 ዕድሜው ከዐምስት እስከ ሃያ ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ሃያ ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ግምቷ ዐሥር ሰቅል ይሁን። 6 ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ ዐምስት ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐምስት ሰቅል ጥሬ ብር፣ ለሴት ከሆነ ሦስት ሰቅል ጥሬ ብር ይሁን። 7 ስድሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐሥራ ዐምስት ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ዐሥር ሰቅል ይሁን። 8 ስእለት የተሳለው ድኻ ከሆነና ግምቱን መክፈል ካልቻለ ግን፣ ለስጦታ ያሰበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የተሳለው ሰው ባለው ዐቅም መሠረት መክፈል የሚገባውን ይተምንለታል። 9 “ ‘ሰውየው የተሳለው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር የተሰጠ እንስሳ የተቀደሰ ይሆናል። 10 ሰውየው መልካም የሆነውን እንስሳ መልካም ባልሆነው፣ መልካም ያልሆነውንም መልካም በሆነው አይለውጥ ወይም አይተካ፤ አንዱን እንስሳ በሌላው ከተካም ሁለቱ የተቀደሱ ይሆናሉ። 11 እንስሳው በሥርዐቱ መሠረት የረከሰ፣ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይገባው ከሆነ፣ ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያቅርብ፤ 12 መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን፣ ካህኑ ዋጋውን ይወስን፤ የካህኑም ውሳኔ የጸና ይሆናል። 13 ባለቤቱ እንስሳውን መዋጀት ከፈለገ ግን፣ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት። 14 “ ‘አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ቢቀድስ፣ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን ካህኑ ዋጋውን ይተምን፤ ካህኑም የተመነው ዋጋ የጸና ይሆናል። 15 ቤቱን የቀደሰው ሰው መልሶ ሊዋጀው ከፈለገ ግን፣ የዋጋውን አንድ ዐምስተኛ በዋጋው ላይ መጨመር አለበት፤ ቤቱም ዳግመኛ የራሱ ይሆናል። 16 “ ‘አንድ ሰው ከወረሰው ርስት ላይ ለእግዚአብሔር የዕርሻ መሬት ቢቀድስ፣ ዋጋው የሚተመነው ለመሬቱ በሚያስፈልገው ዘር መጠን ይሆናል፤ ይኸውም ለአንድ ሆሜር መስፈሪያ የገብስ ዘር ዐምሳ ሰቅል ጥሬ ብር ነው። 17 ሰውየው ዕርሻውን የቀደሰው በኢዮቤልዩ ዓመት ከሆነ፣ የተወሰነው ዋጋ አይለወጥም። 18 ዕርሻውን የሚቀድሰው ከኢዮቤልዩ በኋላ ከሆነ ግን፣ ካህኑ ዋጋውን የሚተምነው እስከሚመጣው የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባሉት ዓመታት ቍጥር ልክ ነው፤ የተተመነውም ዋጋ ይቀነሳል። 19 ዕርሻውን የቀደሰው ሰው መልሶ መዋጀት ከፈለገ፣ በዋጋው ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት፤ ከዚያ በኋላ ዕርሻው እንደ ገና የራሱ ይሆናል። 20 ዕርሻውን ባይዋጅ ወይም ለሌላ ሰው አሳልፎ ቢሸጥ፣ ከዚያ በኋላ ሊዋጀው አይችልም። 21 ዕርሻው በኢዮቤልዩ በሚለቀቅበት ጊዜ ለእግዚአብሔር እንደ ተሰጠ ዕርሻ ተቈጥሮ ቅዱስና የካህናቱ ንብረት ይሆናል። 22 “ ‘አንድ ሰው የወረሰው ርስት ያልሆነውን፣ በገንዘቡ የገዛውን የዕርሻ መሬት ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፣ 23 ካህኑ የዕርሻውን መሬት ዋጋ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ መጠን ይተምናል፤ ሰውየው የተተመነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ አድርጎ በዚያ ዕለት ይክፈል። 24 በኢዮቤልዩ ዓመትም የዕርሻው መሬት የቀድሞው ባለርስት ለነበረው፣ ለሸጠውም ሰው ይመለሳል። 25 እያንዳንዱ ዋጋ የሚተመነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ ሆኖ አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው። 26 “ ‘የእንስሳት በኵር ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንም ሰው የእንስሳትን በኵር ለእግዚአብሔር መቀደስ አይችልም፤ በሬም ሆነ በግ የእግዚአብሔር ነውና። 27 እንስሳው ርኩስ ከሆነ ግን፣ ባለቤቱ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ ዐምስተኛ ጨምሮ ሊዋጀው ይችላል፤ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተተመነው ዋጋ ይሸጥ። 28 “ ‘ነገር ግን ለእግዚአብሔር የተሰጠ፣ ማንኛውም ነገር ሰውም ሆነ እንስሳ ወይም በውርስ የተገኘ መሬት አይሸጥም፤ አይዋጅምም። ለእግዚአብሔር የተሰጠ ማንኛውም ነገር እጅግ የተቀደሰ ነውና። 29 “ ‘እንዲጠፋ የተወሰነ ማንኛውም ሰው አይዋጅም፤ መገደል አለበት። 30 “ ‘ከዕርሻ ምርትም ሆነ ከዛፍ ፍሬ፣ ማንኛውም ከምድሪቱ የሚገኝ ዐሥራት የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነው። 31 አንድ ሰው ከዐሥራቱ የትኛውንም መዋጀት ቢፈልግ፣ በዋጋው ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት። 32 ከቀንድ ከብቶች፣ ከበጎችና ከፍየሎች መንጋ የሚወጣው ዐሥራት ከእረኛ በትር በታች ከሚያልፉት ዐሥረኛው እንስሳ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 33 ሰውየው መልካም የሆነውን መልካም ካልሆነው አይለይ ወይም አይተካ፤ አንዱን በሌላው ቢተካ ግን ሁለቱም እንስሳት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ ሊዋጁም አይችሉም።’ ” 34 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ትእዛዞች እነዚህ ናቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.