ዘሌዋውያን 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበ እግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ ዘይትና ኅብስት 24፥1-3 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥20-21 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲያበሩ ለመብራቱ የሚሆን ከወይራ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው። 3 አሮንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ታቦት መጋረጃ ውጭ በእግዚአብሔር ፊት ያሉትን መብራቶች ከምሽት እስከ ንጋት ያለ ማቋረጥ ያሰናዳቸው፤ ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ሥርዐት ነው። 4 በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ ያሉት መብራቶች ያለ ማቋረጥ መሰናዳት አለባቸው። 5 “የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ እያንዳንዱ ኅብስትም በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ይጋገር። 6 እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ረድፍ በእግዚአብሔር ፊት ባለው የንጹሕ ወርቅ ጠረጴዛ ላይ አኑራቸው። 7 ከኅብስቱ ጋራ የመታሰቢያ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት እንዲሆን ንጹሕ ዕጣን በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ አኑር። 8 ኅብስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ይወክል ዘንድ ዘወትር በየሰንበቱ በእግዚአብሔር ፊት ይደርደር፤ ይህም የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። 9 ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።” እግዚአብሔርን መስደብ የሚያስከትለው ቅጣት 10 እናቱ እስራኤላዊት፣ አባቱ ግብጻዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጣ፤ በሰፈርም ውስጥ ከአንድ እስራኤላዊ ጋራ ተጣሉ። 11 የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን ስም በማቃለል ሰደበ፤ ስለዚህም ወደ ሙሴ አመጡት፤ የሰውየው እናት ስም ሰሎሚት ነበር፤ እርሷም ከዳን ወገን የተወለደው የደብራይ ልጅ ነበረች። 12 የእግዚአብሔር ፈቃድም ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት። 13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 14 “ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው። 15 እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል። 16 የእግዚአብሔርን ስም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ማኅበሩ ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ የእግዚአብሔርን ስም ከሰደበ ይገደል። 17 “ ‘ሰውን ደብድቦ የገደለ ይገደል። 18 የሌላውን ሰው እንስሳ ደብድቦ የገደለ ማንኛውም ሰው ያንኑ ዐይነት እንስሳ ይተካለት። 19 ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጕዳት ቢያደርስ፣ የዚያው ዐይነት ጕዳት ይፈጸምበት፤ 20 ይኸውም ስብራት በስብራት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ ማለት ነው። በሌላው ሰው ላይ ያደረሰው ጕዳት በርሱም ላይ ይድረስበት፤ 21 እንስሳ የገደለ ማንኛውም ሰው በገደለው ፈንታ ይተካ፤ ሰው የገደለ ግን ይገደል። 22 ለመጻተኛው ሆነ ለአገር ተወላጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይኑራችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” 23 ሙሴም ይህን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ እነርሱም ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወገሩት፤ እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.