ዘሌዋውያን 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምትዋጇቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። ሰንበት 3 “ ‘ሥራ የምትሠሩበት ስድስት ቀን አላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት፣ የተቀደሰ ጉባኤ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር ሰንበት ስለ ሆነ፣ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩበት። የፋሲካና የቂጣ በዓል 23፥4-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20 ፤ ዘኍ 28፥16-25 ፤ ዘዳ 16፥1-8 4 “ ‘የተመረጡ የእግዚአብሔር በዓላት ብላችሁ በተወሰኑላቸው ጊዜያት የምታውጇቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እነዚህ ናቸው፤ 5 የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የእግዚአብሔር ፋሲካ በዓል ይጀመራል። 6 በዚያው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ለሰባት ቀንም ቂጣ ብሉ። 7 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አታከናውኑ። 8 ሰባት ቀን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ በዚያ ዕለት የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑ።’ ” የበኵራት ስጦታ በዓል 9 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ከሰበሰባችሁት እህል የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ አቅርቡ፤ 11 ነዶው ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዘው፤ ካህኑ ነዶውን የሚወዘውዘው በሰንበት ቀን ማግስት ነው። 12 ነዶውን በምትወዘውዙበት ቀን እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ 13 ከዚህም ጋራ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ለእህል ቍርባን፣ አንድ አራተኛ የሂን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን አቅርቡ። 14 ስጦታውን ለአምላካችሁ እስከምታቀርቡበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ እንጀራም ቢሆን ቈሎ ወይም እሸት አትብሉ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው። የመከር በዓል 23፥15-22 ተጓ ምብ – ዘኍ 28፥26-31 ፤ ዘዳ 16፥9-12 15 “ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቍጠሩ። 16 እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ ዐምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 17 በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር አምጡ። 18 ከእንጀራውም ጋራ ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት እንከን የሌለው ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። 19 እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ። 20 ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋራ የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው። 21 በዚያ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው። 22 “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” የመለከት በዓል 23፥23-25 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥1-6 23 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በመለከት ድምፅም የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ። 25 መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ” የስርየት ቀን 23፥26-32 ተጓ ምብ – ዘሌ 16፥2-34 ፤ ዘኍ 29፥7-11 26 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 27 “የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 28 በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለ ሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ። 29 በዚያ ዕለት ሰውነቱን የማያጐሳቍል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 30 በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 31 ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው። 32 ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።” የዳስ በዓል 23፥33-43 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥12-39 ፤ ዘዳ 16፥13-17 33 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 34 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቈያል። 35 የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት። 36 ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት። 37 “ ‘የሚቃጠል መሥዋዕትንና የእህል ቍርባንን፣ መሥዋዕትንና የመጠጥ ቍርባንን በተመደበላቸው ቀን ለእግዚአብሔር በእሳት ለማቅረብ፣ የተቀደሱ ጉባኤዎችን የምታውጁባቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38 እነዚህ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር ሰንበት ከምታቀርቡት፣ ከስጦታችሁ፣ ከስእለታችሁና ከበጎ ፈቃድ ስጦታችሁ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ስጦታዎች ናቸው። 39 “ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል። 40 በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 41 በየዓመቱም የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት። 42 ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤ 43 በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” 44 በዚህ ሁኔታም ሙሴ የተመረጡትን የእግዚአብሔር በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.