Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘሌዋውያን 22 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “እስራኤላውያን ቀድሰው ለእኔ የለዩትን ቅዱስ መሥዋዕት በአክብሮት ባለመያዝ፣ ቅዱስ ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

3 “እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፣ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ መሥዋዕት ቢቀርብ ያ ሰው ከፊቴ ይወገድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

4 “ ‘ከአሮን ዘር ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበት ወይም ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ማንኛውም ሰው እስኪነጻ ድረስ ቅዱሱን መሥዋዕት አይብላ፤ እንዲሁም በአስከሬን የረከሰውን ነገር ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበትን ሰው ቢነካ፣

5 ወይም በደረቱ የሚሳብ የሚያረክስ ነገርን ወይም የሚያረክስ ማንኛውንም ሰው ቢነካ፣ የቱንም ዐይነት ርኩሰት ቢሆን፣

6 እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።

7 ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ የተቀደሰውን መሥዋዕት መብላት ይችላል፤ ምግቡ ነውና።

8 እንዳይረክስ ማንኛውንም ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

9 “ ‘ካህናት ትእዛዞቼን በመናቅ በደለኛ እንዳይሆኑና እንዳይሞቱ ይጠብቋቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

10 “ ‘ከካህን ቤተ ሰብ በቀር የካህኑ እንግዳም ሆነ ቅጥር ሠራተኛ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።

11 ነገር ግን ካህኑ በገንዘብ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ ባሪያ ቢኖረው፣ ያ ባሪያ ከካህኑ ድርሻ መብላት ይችላል።

12 የካህን ልጅ፣ ካህን ያልሆነ ሌላ ሰው ካገባች፣ ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አትችልም።

13 ይሁን እንጂ የካህኑ ልጅ ባሏ ቢሞት ወይም ብትፋታ፣ ልጆችም ባይኖሯትና እንደ ልጅነት ጊዜዋ በአባቷ ቤት ለመኖር ብትመለስ፣ ከአባቷ ድርሻ መብላት ትችላለች፤ ያልተፈቀደለት ሰው ግን ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አይችልም።

14 “ ‘ማንኛውም ሰው ባለማወቅ የተቀደሰውን መሥዋዕት ቢበላ፣ የመሥዋዕቱን አንድ ዐምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይተካ።

15 እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን የተቀደሰ መሥዋዕት ካህናቱ አያርክሱት፤

16 ይህንኑ የተቀደሰ መሥዋዕት እንዲበሉና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽሙ አያድርጉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”


ለእግዚአብሔር መቅረብ የማይገባው መሥዋዕት

17 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

18 “ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ከእናንተ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ቢሆን፣

19 መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው ከላም ወገን ወይም ከበጎች ወይም ከፍየሎች እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ።

20 እንከን ያለበትን ማንኛውንም ነገር አታቅርቡ፤ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት አይኖረውምና።

21 ማንኛውም ሰው ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ከላም ወይም ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት ሲያቀርብ፣ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ፍጹም የሆነውንና እንከን የሌለበትን ያቅርብ።

22 ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም ማንኛውንም ዐይነት እከክ ወይም ቋቍቻ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ ከእነዚህ መካከል የትኛውንም በመሠዊያው ላይ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ።

23 አካሉ ከመጠን በላይ የረዘመን ወይም ያጠረን በሬ ወይም በግ የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጋችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ይሁን እንጂ ስእለት ለመፈጸም ተቀባይነት አይኖረውም።

24 አባለዘሩ የተቀጠቀጠ ወይም የተኰላሸ፣ የተሰነጠቀ ወይም የተቈረጠ ማንኛውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህንም በምድራችሁ አትሠዉ።

25 እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ከባዕዳን በመቀበል ለአምላካችሁ ምግብ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ ነውር ስላለባቸው ፍጹም አይደሉምና ተቀባይነት አይኖራቸውም።’ ”

26 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

27 “ጥጃ ወይም የበግ ግልገል ወይም የፍየል ግልገል በሚወለድበት ጊዜ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋራ ይቈይ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ግን ተቀባይነት ያለው ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ይሆናል።

28 ላምን ከጥጃዋ፣ በግንም ከግልገሏ ጋራ በአንድ ቀን አትረዱ።

29 “ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጋችሁ አቅርቡት።

30 መሥዋዕቱ በዚያ ዕለት ይበላ፤ ለሚቀጥለውም ቀን አታሳድሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

31 “ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ አድርጓቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

32 ቅዱሱን ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ቅዱስ መሆኔ በእስራኤላውያን ዘንድ ይታወቅ፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

33 አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告