Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘሌዋውያን 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ለካህናት የተሰጠ መመሪያ

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ማንኛውም ሰው ከዘመዶቹ መካከል ስለ ሞተው ሰው ራሱን አያርክስ፤

2 ነገር ግን የቅርብ ዘመዶቹ ስለ ሆኑት እናቱ፣ አባቱ፣ ወንድ ልጁ፣ ሴት ልጁ፣ ወይም ወንድሙ፣

3 እንዲሁም ባለማግባቷ ከርሱ ጋራ ስለምትኖር እኅቱ ራሱን ሊያረክስ ይችላል።

4 ከርሱ ጋራ በጋብቻ ለሚዛመዱት ግን ራሱን አያርክስ።

5 “ ‘ካህናት ዐናታቸውን አይላጩ፤ የጢማቸውን ዙሪያ አይላጩ፤ ሰውነታቸውንም አይንጩ፤

6 ለአምላካቸው የተቀደሱ ይሁኑ፤ የአምላካቸውንም ስም አያርክሱ። ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበውን መሥዋዕት የአምላካቸውን ምግብ ስለሚያቀርቡ ቅዱሳን ይሁኑ።

7 “ ‘ካህናት በዝሙት የረከሱትንም ሆነ ከባሎቻቸው የተፋቱትን ሴቶች አያግቡ፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ናቸውና።

8 የአምላክህን ምግብ የሚያቀርብ ነውና ቀድሰው፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና ቅዱስ ይሁንላችሁ።

9 “ ‘የካህን ሴት ልጅ ዝሙት ዐዳሪ ሆና ራሷን ብታረክስ፣ አባቷን ታዋርዳለች፤ በእሳት ትቃጠል።

10 “ ‘ከወንድሞቹ መካከል ተለይቶ በራሱ ላይ ዘይት የፈሰሰበትና የክህነት ልብስ እንዲለብስ የተቀባው ካህን የራስ ጠጕሩን አይንጭ፤ ወይም ልብሱን አይቅደድ።

11 አስከሬን ወዳለበት ስፍራ አይግባ፤ ስለ አባቱም ሆነ ስለ እናቱ ራሱን አያርክስ፤

12 የተቀደሰበት የአምላኩ የቅብዐት ዘይት በላዩ ስለ ሆነ የአምላኩን መቅደስ ትቶ በመሄድ መቅደሱን አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

13 “ ‘ካህኑ የሚያገባት ሴት ድንግል ትሁን።

14 ባል የሞተባትን፣ የተፋታችውን ወይም በዝሙት ዐዳሪነት የረከሰችውን ሴት አያግባ፤ ነገር ግን ከወገኖቹ መካከል ድንግሊቱን ያግባ።

15 በወገኖቹ መካከል ዘሩን አያርክስ። እርሱን የምቀድሰው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

16 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

17 “አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ እንከን ያለበት ማንኛውም ሰው የአምላኩን ምግብ ይሠዋ ዘንድ አይቅረብ።

18 ዕውር ወይም ዐንካሳ፣ የፊቱ ገጽታ ወይም የሰውነቱ ቅርጽ የተበላሸ ማንኛውም የአካል ጕድለት ያለበት ሰው አይቅረብ።

19 እንዲሁም እግሩ ወይም እጁ ሽባ የሆነ፣

20 ጐባጣ ወይም ድንክ፣ ማንኛውም ዐይነት የዐይን እንከን ያለበት፣ የሚያዥ ቍስል ወይም እከክ ያለበት ወይም ጃንደረባ አይቅረብ።

21 ከካህኑ ከአሮን ዘር ማንኛውም ዐይነት የአካል ጕድለት ያለበት ሰው ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ሊያቀርብ አይምጣ፤ እንከን ያለበት ስለ ሆነ፣ የአምላኩን ምግብ ለማቅረብ አይምጣ።

22 እርሱም የተቀደሰውንና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የአምላኩን ምግብ ይብላ።

23 ነገር ግን እንከን ያለበት ስለ ሆነ መቅደሴን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይቅረብ ወይም ወደ መሠዊያው አይጠጋ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

24 ሙሴም ይህን ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን ሁሉ ነገራቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告