ዘሌዋውያን 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየእህል ቍርባን 1 “ ‘ማንኛውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ዱቄቱ የላመ ይሁን፤ ዘይት ያፍስስበት፤ ዕጣንም ይጨምርበት፤ 2 ወደ ካህናቱም ወደ አሮን ልጆች ያምጣው። ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ሙሉ ያንሣለት፤ ዕጣኑንም ሁሉ ይውሰደው፤ ይህንም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። 3 የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው። 4 “ ‘በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ የእህል ቍርባን በምታቀርብበት ጊዜ፣ ከላመ ዱቄት ተዘጋጅቶ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ኅብስት ይሁን፤ አለዚያም ያለ እርሾ በሥሡ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ ይሁን። 5 የእህል ቍርባንህ በምጣድ የሚጋገር ከሆነ፣ እርሾ ሳይገባበት በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6 ቈራርሰህ ዘይት አፍስስበት፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 7 የእህል ቍርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ። 8 በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤ 9 ካህኑም ከእህሉ ቍርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10 የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው። 11 “ ‘ለእግዚአብሔር በእሳት በምታቀርቡት ቍርባን ውስጥ እርሾ ወይም ማር ጨምራችሁ ማቃጠል ስለማይገባችሁ፣ በምታቀርቡት በማንኛውም የእህል ቍርባን እርሾ አይኑርበት። 12 እነዚህን የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሽታው ደስ የሚያሰኝ ቍርባን ሆነው በመሠዊያ ላይ ለመቃጠል አይቀርቡም። 13 የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ቀምመው፤ የአምላክህ የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አይታጣ፤ በቍርባንህም ላይ ጨው ጨምርበት። 14 “ ‘የእህል በኵራት ቍርባን ለእግዚአብሔር በምታመጣበት ጊዜ፣ የተፈተገና በእሳት የተጠበሰ እሸት አቅርብ። 15 ዘይት ጨምርበት፤ ዕጣንም በላዩ አስቀምጥ፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 16 ካህኑም ከተፈተገው እህልና ከዘይቱ ወስዶ፣ ከዕጣኑ ሁሉ ጋራ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መታሰቢያ አድርጎ ያቃጥል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.