ዘሌዋውያን 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምደም መብላት ስለ መከልከሉ 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ለአሮንና ለልጆቹ፣ ለእስራኤላውያንም ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ 3 ማንኛውም እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ወይም ከሰፈር ውጭ በሬ፣ በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፣ 4 በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፣ ያ ሰው በከንቱ ደም እንዳፈሰሰ ይቈጠራል፤ ደም በማፍሰሱም ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። 5 እስራኤላውያን የሚሠዉትን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር የሚያመጡበት ምክንያት ይህ ነው። ይህንም ካህኑ ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥተው ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት በማድረግ ያቅርቡ። 6 ካህኑም ደሙን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይርጭ፤ ሥቡንም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሽታ እንዲሆን ያቃጥል። 7 ከዚህ በፊት ላመነዘሩባቸው አጋንንት ከእንግዲህ ወዲህ ማንኛውንም መሥዋዕት ሊሠዉ አይገባም። ይህ ለእነርሱና ከእነርሱ በኋላ ለሚነሣው ትውልድ ሁሉ የዘላለም ሥርዐት ይሁን።’ 8 “እንዲህም በላቸው፤ ‘የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ፣ 9 ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር ባያቀርብ፣ ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። 10 “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ 11 የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ፤ ለሰውም ሕይወት ስርየት የሚያስገኝ ደም ነው። 12 ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “ከእናንተ ማንም ደም አይብላ፤ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛም ቢሆን ደም አይብላ” አልሁ። 13 “ ‘እንዲበላ የተፈቀደውን ማንኛውንም እንስሳ ወይም ወፍ ዐድኖ የያዘ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደሙን ከውስጡ ያፍስስ፤ ዐፈርም ያልብሰው፤ 14 የማንኛውም ፍጡር ሕይወት ደሙ ነውና። ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “የፍጡር ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የማንኛውንም ፍጡር ደም አትብሉ፤ የበላው ሰው ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ” አልኋቸው። 15 “ ‘ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን የበላ ማንኛውም የአገር ተወላጅ ወይም መጻተኛ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16 ልብሱን ባያጥብ፣ ሰውነቱንም ባይታጠብ ግን ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.