ዘሌዋውያን 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሚያረክስ የሰውነት ፈሳሽ 1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብላችሁ ንገሯቸው፤ ‘ማንም ሰው ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ቢወጣ ያ ሰው ርኩስ ነው። 3 ከሰውነቱ የሚወጣው ፈሳሽ መፍሰሱን ቢቀጥል ወይም ባይቀጥል ሰውየው ርኩስ ነው፤ ፈሳሹም ርኩሰት የሚያስከትለው እንደዚህ ነው፤ 4 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የተኛበት የትኛውም መኝታ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ የተቀመጠበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል። 5 ዐልጋውን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 6 ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው በተቀመጠበት በየትኛውም ነገር ላይ የተቀመጠ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 7 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣውን ሰው የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 8 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ቢተፋ፣ የተተፋበት ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 9 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ 10 ከበታቹ ያለውንም ነገር ሁሉ የነካ ማንም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ማንም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 11 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው እጁን በውሃ ሳይታጠብ ሌላውን ሰው ቢነካ፣ የተነካው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 12 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የነካው የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ከዕንጨት የተሠራ ዕቃ ከሆነ በውሃ ይታጠብ። 13 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ከፈሳሹ ሲነጻ፣ በሕጉ መሠረት ለመንጻቱ ሰባት ቀን ይቍጠር፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በምንጭ ውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዞ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ። 15 ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሹ በእግዚአብሔር ፊት ለሰውየው ያስተሰርይለታል። 16 “ ‘አንድ ሰው ዘሩ በሚፈስስበት ጊዜ ሰውነቱን በሙሉ በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 17 የፈሰሰው ዘር የነካው ማንኛውም ልብስ ወይም ቍርበት በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 18 አንድ ሰው ከአንዲት ሴት ጋራ ግብረ ሥጋ ፈጽሞ ዘር ቢፈስሰው፣ ሁለቱም በውሃ ይታጠቡ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩሳን ይሆናሉ። 19 “ ‘ሴት ጊዜውን እየጠበቀ የሚመጣው የደም መፍሰስ ቢኖርባት፣ የወር አበባዋ ርኩሰት እስከ ሰባት ቀን ይቈያል፤ በዚህ ጊዜ ማንም ሰው ቢነካት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 20 “ ‘በወር አበባዋ ጊዜ የምትተኛበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ የተቀመጠችበትም ነገር ርኩስ ይሆናል። 21 መኝታዋን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 22 የተቀመጠችበትን ማንኛውንም ነገር የነካ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል፤ 23 መኝታዋን ወይም የተቀመጠችበትን ማንኛውንም ነገር የነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 24 “ ‘አንድ ሰው ከርሷ ጋራ ቢተኛና የወር አበባዋ ቢነካው፣ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። 25 “ ‘ሴት ከወር አበባዋ ጊዜ ሌላ ብዙ ቀን ደም ቢፈስሳት፣ ወይም የወር አበባዋ ጊዜ ካለፈ በኋላ የደሙ መፍሰስ ባይቋረጥ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ፣ ደም መፍሰሱ እስኪቆም ድረስ ርኩስ ትሆናለች። 26 ደሟ መፍሰሱን በቀጠለበት ጊዜ ሁሉ፣ የምትተኛበት ማንኛውም መኝታ ልክ በወር አበባዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ርኩስ ይሆናል፤ የምትቀመጥበትም ማንኛውም ነገር ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ርኩስ ይሆናል። 27 እነዚህንም የሚነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 28 “ ‘ከደሟ ፍሳሽ ሳትነጻ ሰባት ቀን ትቍጠር፤ ከዚያም በኋላ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ትሆናለች። 29 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዛ በመቅረብ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለካህኑ ትሰጣለች። 30 ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሿ ርኩሰት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል። 31 “ ‘በመካከላቸው ያለችውን ማደሪያዬን እንዳያረክሱና በርኩሰታቸው እንዳይሞቱ፣ እስራኤላውያንን ከሚያረክሳቸው ነገር ለዩአቸው።’ ” 32 ፈሳሽ ነገር የሚወጣውን፣ ዘሩም በመፍሰሱ ርኩስ የሆነውን ሰው ሁሉ፣ 33 በወር አበባ ላይ ያለችን ሴት፣ ፈሳሽ ነገር የሚወጣቸውን ወንድ ወይም ሴት፣ በሥርዐቱ መሠረት ርኩስ ከሆነች ሴት ጋራ የሚተኛውን ወንድ በሚመለከት ሕጉ ይኸው ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.