ዘሌዋውያን 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምተላላፊ የቈዳ በሽታ 1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2 “ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቈዳ ላይ ዕብጠት ወይም ችፍታ ወይም ቋቍቻ ቢወጣበትና ይህም ወደ ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚለወጥበት ከሆነ፣ ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3 ካህኑም በሰውየው ቈዳ ላይ ያለውን ቍስል ይመርምር፤ በቍስሉ በተበከለው አካባቢ ያለው ጠጕር ወደ ነጭነት ተለውጦ ቢያገኘውና ቦታው ጐድጕዶ ወደ ውስጥ ቢገባ፣ ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ ይህን ባወቀ ጊዜ፣ ሰውየው በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ርኩስ መሆኑ ይገለጽ። 4 በቈዳው ላይ ያለው ቋቍቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ፣ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጕር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው። 5 በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቍስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው። 6 በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቍስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቍስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 7 ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤ 8 ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 9 “ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤ 10 ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጕሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣ 11 ሥር የሰደደ የቈዳ በሽታ ነውና ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ርኩስ መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነም ሰውየውን አያግልለው። 12 “ደዌው በአካላቱ ሁሉ ላይ በመውጣት በሽተኛውን ከራስ ጠጕር እስከ እግር ጥፍር ያለበሰው መሆኑን ካህኑ እስካየ ድረስ፣ 13 ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው የሰውየውን ሰውነት ሙሉ በሙሉ ሸፍኖት ከተገኘ፣ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሙሉ በሙሉ ነጭ ስለ ሆነ ንጹሕ ነው፤ 14 ነገር ግን ቍስሉ አመርቅዞ ቀይ ሥጋ ቢታይበት ርኩስ ይሁን። 15 ካህኑም የተገለጠውን ቀይ ሥጋ በሚያይበት ጊዜ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቀይ ሥጋ ርኩስ ስለ ሆነ፣ ተላላፊ በሽታ ነው። 16 ቀይ ሥጋ ተለውጦ ከነጣ ግን ወደ ካህኑ ይሂድ፤ 17 ካህኑም ይመርምረው፤ ቍስሎች ወደ ነጭነት ተለውጠው ከተገኙ፣ የታመመው ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ንጹሕም ይሆናል። 18 “አንድ ሰው በገላው ላይ ዕባጭ ወጥቶ ቢድን፣ 19 ዕባጩ በነበረበት ቦታ ላይም ነጭ ዕብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቍቻ ቢታይ፣ ካህኑ ዘንድ ይቅረብ። 20 ካህኑም ይመርምረው፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ የገባ ቢሆን በቦታውም ያለው ጠጕር ቢነጣ፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 21 ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር በውስጡ ከሌለ፣ ዘልቆ ካልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰባት ቀን ያግልለው። 22 በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ካገኘውም፣ ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚተላለፍ ነው። 23 ቋቍቻው ግን ባለበት ከቈየና ወደ ሌላ ስፍራ ካልተስፋፋ፣ የዕባጩ ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። 24 “አንድ ሰው እሳት ቈዳውን ቢያቃጥለውና በተቃጠለው ስፍራ ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቍቻ ቢታይበት፣ 25 ካህኑ ይመርምረው፤ ቋቍቻው ባለበትም ቦታ ያለው ጠጕር ቢነጣና ከቈዳው በታች ዘልቆ ቢገባ፣ በቃጠሎው ሰበብ ከውስጥ የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው፤ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 26 ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር የሌለበት፣ ከቈዳውም በታች ዘልቆ ያልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። 27 በሰባተኛው ቀን ካህኑ ይመርምረው፤ በሽታውም በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ቢያገኘው፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 28 ቋቍቻ ባለበት ከቈየና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ይልቁንም እየከሰመ ከሄደ፣ በቃጠሎው ሰበብ የተከሠተ ዕብጠት ነውና ካህኑ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ የቃጠሎው ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም። 29 “በወንድ ወይም በሴት ዐናት ወይም አገጭ ላይ ቍስል ቢወጣ፣ 30 ካህኑ ቍስሉን ይመርምር፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ ከገባ፣ በውስጡም ያለው ጠጕር ቢጫና ቀጭን ከሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚያሳክክ የራስ ወይም የአገጭ ተላላፊ በሽታ ነው። 31 ካህኑ እንዲህ ዐይነቱን ቍስል በሚመረምርበት ጊዜ፣ ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባና በውስጡም ጥቍር ጠጕር ከሌለ፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። 32 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቍስሉን ይመርምር፤ የሚያሳክከው ቦታ ያልሰፋ፣ ቢጫ ጠጕር የሌለውና ከቈዳው በታች ዘልቆ ያልገባ ከሆነ፣ 33 ከቈሰለው ቦታ በቀር ጠጕሩን ይላጭ፤ ካህኑ ሰባት ተጨማሪ ቀን ሰውየውን ያግልል። 34 ካህኑ በሰባተኛው ቀን የሚያሳክከውን የሰውየውን ቍስል ይመርምር፤ በቈዳው ላይ ካልሰፋና ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባ ካህኑ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ልብሱን ዐጥቦ ንጹሕ ይሁን። 35 ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ግን የሚያሳክከው ቍስል ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ 36 ካህኑ ይመርምረው፤ ቍስሉ በቈዳው ላይ ከሰፋ፣ ካህኑ የጠጕሩን ቢጫ መሆን አለመሆን ማየት አያሻውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው። 37 ነገር ግን ቍስሉ በካህኑ አመለካከት ለውጥ ያላሳየ ከሆነና በውስጡ ጥቍር ጠጕር ካበቀለ ቍስሉ ድኗል፤ ሰውየው ነጽቷል፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። 38 “በወንድ ወይም በሴት ቈዳ ላይ ቋቍቻ ቢወጣ፣ 39 ካህኑ ይመርምራቸው፤ ቋቍቻው ዳለቻ ከሆነ፣ በቈዳ ላይ የወጣ ጕዳት የማያስከትል ችፍታ ነው፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው። 40 “አንድ ሰው የራሱ ጠጕር ከዐናቱ ዐልቆ መላጣ ቢሆን ንጹሕ ነው። 41 ጠጕሩ ከፊት ለፊት ተመልጦ ራሰ በራ ቢሆንም ንጹሕ ነው። 42 ነገር ግን በመላጣው ወይም በበራው ላይ ነጣ ያለ ቀይ ቍስል ቢወጣበት፣ ያ ከመላጣው ወይም ከበራው የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው። 43 ካህኑ ይመርምረው፤ በመላጣው ወይም በበራው ላይ ያበጠው ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚመስል ነጣ ያለ ቍስል ከሆነ፣ 44 ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኩስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቍስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 45 “እንዲህ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የተቀደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጕሩን ይግለጥ፤ እስከ አፍንጫውም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46 ተላላፊ በሽታው እስካለበት ጊዜ ድረስ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጥ፤ ከሰፈር ውጪም ይኑር። በልብስ ላይ የሚታይ ተላላፊ በሽታ 47 “ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣ 48 በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጕር ወይም የበፍታ ልብስ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣ 49 በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለ ሆነ ካህኑ ይየው። 50 ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል። 51 በሰባተኛውም ቀን ይመርምረው፤ ደዌው በልብሱ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ወይም ለማንኛውም አገልግሎት በሚውል ዐጐዛ ላይ ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ክፉ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው። 52 ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል። 53 “ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ፣ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ተስፋፍቶ ካልተገኘ፣ 54 ካህኑ ደዌው ያለበት ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ዕቃውንም ሰባት ቀን ደግሞ ያግልል። 55 ደዌው ያለበት ዕቃ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው ባይስፋፋም እንኳ መልኩን ካልለወጠ፣ ርኩስ ነው፤ ደዌው የወጣው በውስጥም ሆነ በውጭ ዕቃው በእሳት ይቃጠል። 56 ዕቃው ከታጠበ በኋላ ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው ከስሞ ቢገኝ፣ በደዌ የተበከለውን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቈዳው ወይም በሸማኔ ዕቃ ከተሠራው ወይም በእጅ ከተጠለፈው ጨርቅ ቀዶ ያውጣ። 57 ነገር ግን ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ቢታይ፣ መስፋፋቱ ስለ ሆነ ደዌው ያለበት ማንኛውም ነገር በእሳት ይቃጠል። 58 ታጥቦ ከደዌ የጠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ እንደ ገና ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።” 59 ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ በደዌ ቢበከል፣ ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለማወቅ ሕጉ ይህ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.