ዘሌዋውያን 12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምከወሊድ በኋላ የመንጻት ሥርዐት 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሴት አርግዛ ወንድ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ትረክሳለች። 3 ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ሸለፈቱን ይገረዝ። 4 ሴትዮዋም ከደሟ እስክትነጻ ድረስ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቈይ፤ የመንጻቷም ወራት እስኪፈጸም ድረስ ማንኛውንም የተቀደሰ ነገር አትንካ፤ ወደ ቤተ መቅደስም አትግባ። 5 ነገር ግን የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ፣ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ሁለት ሳምንት ትረክሳለች፤ ከዚያም ከደሟ እስክትነጻ ስድሳ ስድስት ቀን ትቈይ። 6 “ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻቷ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ። 7 ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቅርበው፤ ያስተስርይላትም፤ ሴትዮዋም ከደሟ ፈሳሽ ትነጻለች። “ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ብትወልድ ሕጉ ይኸው ነው። 8 ጠቦት ለማምጣት ዐቅሟ ካልፈቀደ፣ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች፣ አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ሌላው ደግሞ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቅርብ፤ በዚህም ካህኑ ያስተሰርይላታል፤ እርሷም ትነጻለች።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.