Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘሌዋውያን 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የተፈቀደና ያልተፈቀደ መብል
11፥1-23 ተጓ ምብ – ዘዳ 14፥3-20

1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፤ ‘በየብስ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ የምትበሏቸው እነዚህ ናቸው፦

3 ሰኰናው የተሰነጠቀውን የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ።

4 “ ‘የሚያመሰኩ ሆነው ሰኰናቸው ያልተሰነጠቀ ወይም ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ሆኖ የማያመሰኩትን አትብሉ፤ ግመል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

5 ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

6 ጥንቸል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

7 ዐሣማ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።

8 የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ፤ ጥንባቸውንም አትንኩ፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሁኑ።

9 “ ‘በባሕሮችና በወንዞች ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን መብላት ትችላላችሁ፤

10 ነገር ግን በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት ሁሉ፣ ከሚንፏቀቁት ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ሌሎች ፍጥረታት መካከል ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ፤

11 በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆኑ ሥጋቸውን አትብሉ፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ፤

12 ክንፍና ቅርፊት የሌለው ማንኛውም በውሃ ውስጥ የሚኖር ፍጡር በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ይሁን።

13 “ ‘ከአዕዋፍ ወገን እነዚህን ትጸየፋላችሁ፤ ጸያፍ ስለ ሆኑም አትብሏቸው፦ ንስር፣ የጥንብ አሞራ፣ ግልገል አንሣ፣

14 ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፣

15 ማንኛውም ዐይነት ቍራ፣

16 ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣

17 ጕጕት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣

18 የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣

19 ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጃንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ።

20 “ ‘ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ።

21 ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ።

22 ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ።

23 ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው።

24 “ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

25 የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።

26 “ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል።

27 አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

28 የእነዚህን በድን የሚያነሣ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንስሳቱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው።

29 “ ‘ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፦ ሙጭልጭላ፣ ዐይጥ፣ እንሽላሊት በየወገኑ፣

30 ዔሊ፣ ዐዞ፣ ገበሎ፣ አርጃኖ፣ ዕሥሥት።

31 ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሁሉ መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ ከእነዚህም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

32 በድኑ በማንኛውም ዕቃ ላይ ቢወድቅ ያ ዕቃ ከዕንጨት፣ ከጨርቅ፣ ከቈዳ ወይም ከበርኖስ የተሠራ ከረጢት ቢሆን ርኩስ ይሆናል፤ በውሃ ውስጥ ይደረግ፤ ሆኖም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።

33 በድኑም በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፣ በውስጡ ያለ ነገር ሁሉ ርኩስ ስለሚሆን ዕቃውን ስበሩት።

34 ማንኛውም ምግብ እንዲህ ካለው ዕቃ ውሃ ቢፈስስበት ይረክሳል፤ ከዚህ ዕቃ የሚጠጣውም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።

35 ከበድናቸው አንዱ የወደቀበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ምድጃም ይሁን ማሰሮ ይሰበር፤ ርኩሳን ናቸው፤ እናንተም ተጸየፏቸው።

36 ነገር ግን ምንጭ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ንጹሕ እንደ ሆነ ይቈያል፤ ሆኖም በድኑን የነካ ይረክሳል።

37 በሚዘራ ዘር ላይ በድን ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ እንደ ሆነ ይቈያል።

38 ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ በድን ቢወድቅበት ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።

39 “ ‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳት አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

40 ማንም ሰው ከበድኑ ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

41 “ ‘ምድር ለምድር የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡር ጸያፍ ነው፤ አይበላም።

42 ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጡር ሁሉ፣ ይኸውም በደረቱ የሚሳበውን ወይም በአራት እግር የሚሄደውን ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን አትብሉ፤ ጸያፍ ነው።

43 በእነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ራሳችሁን አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነርሱም ራሳችሁን በማጕደፍ አትርከሱ።

44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ተለዩ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ ምድር ለምድር በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ፍጡር ራሳችሁን አታርክሱ።

45 አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።

46 “ ‘እንስሳትንና አዕዋፍን፣ በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ሁሉ በሚመለከት የተሰጠ ሕግ ይህ ነው።

47 በዚህም በርኩሱና በንጹሑ መካከል፣ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጥረታት የሚበሉትንና የማይበሉትን ትለያላችሁ።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告