Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘሌዋውያን 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የናዳብና የአብዩድ መሞት

1 የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ።

2 ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ።

3 ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር፦ “ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣ እከበራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ።

4 ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልዳፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው።

5 እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።

6 ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ ጠጕራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ።

7 የእግዚአብሔር የመቅቢያ ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን አትውጡ።” እነርሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።

8 እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ አለው፤

9 “እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።

10 የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኩሱንና ንጹሑን ለዩ፤

11 እግዚአብሔርም በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።”

12 ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር ከቀረበው የእህል ቍርባን የቀረውን ወስዳችሁ ቂጣ ጋግሩ፤ እጅግ ቅዱስ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት።

13 ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት ያንተና የልጆችህ ድርሻ ይህ ስለ ሆነ፣ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት፤ እንዲህ ታዝዣለሁና።

14 ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የእናንተ ድርሻ ሆኖ ስለ ተሰጠ፣ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ብሉት።

15 የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋራ ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”

16 ሙሴ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበውን ፍየል አጥብቆ ፈለገ፤ መቃጠሉንም በተረዳ ጊዜ የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤

17 “የኀጢአት መሥዋዕቱን ለምን በተቀደሰው ስፍራ አልበላችሁትም? እጅግ የተቀደሰ ነው፤ በእግዚአብሔር ፊት ስርየት በማስገኘት የሕዝቡን ኀጢአት እንድታስወግዱበት የተሰጣችሁ ነበር፤

18 ደሙ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ስላልገባ፣ በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት ፍየሉን በተቀደሰው ስፍራ መብላት ይገባችሁ ነበር።”

19 አሮንም ሙሴን፣ “እነሆ፤ በዛሬው ቀን የኀጢአት መሥዋዕታቸውንና የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ እኔም እንዲህ ያለ ነገር የደረሰብኝ ሰው ነኝ፤ ታዲያ፣ ዛሬ የኀጢአት መሥዋዕቱን ብበላ ኖሮ እግዚአብሔርስ ደስ ይለው ኖሯልን?” አለው።

20 ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告