ሰቈቃወ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምא አሌፍ א አሌፍ 1 ወርቁ እንዴት ደበሰ! ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የከበሩ ድንጋዮች፣ በየመንገዱ ዳር ተበታትነዋል። ב ቤት ב ቤት 2 እንደ ወርቅ ይቈጠሩ የነበሩ፣ የከበሩ የጽዮን ወንዶች ልጆች፣ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው፣ እንዴት አሁን እንደ ሸክላ ዕቃ ሆኑ! ג ጊሜል ג ጊሜል 3 ቀበሮዎች እንኳን ግልገሎቻቸውን ለማጥባት፣ ጡታቸውን ይሰጣሉ፤ ሕዝቤ ግን በምድረ በዳ እንዳሉ ሰጎኖች፣ ጨካኞች ሆኑ። ד ዳሌት ד ዳሌት 4 ከውሃ ጥም የተነሣ፣ የሕፃናት ምላስ ከላንቃቸው ጋራ ተጣበቀ፤ ልጆቹ ምግብ ለመኑ፤ ነገር ግን ማንም አልሰጣቸውም። ה ሄ ה ሄ 5 ምርጥ ምግብ ይበሉ የነበሩ፣ ተቸግረው በየመንገዱ ላይ ተንከራተቱ፤ ሐምራዊ ግምጃ ለብሰው ያደጉ፣ አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተኙ። ו ዋው ו ዋው 6 በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት፣ የማንም እጅ ሳይረዳት፣ በድንገት ከተገለበጠችው፣ ሰዶም ላይ ከደረሰው ቅጣት ይልቅ ታላቅ ነው። ז ዛይን ז ዛይን 7 መሳፍንታቸው ከበረዶ ይልቅ ብሩህ፣ ከወተትም ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ሰውነታቸው ከቀይ ዕንቍ የቀላ፣ መልካቸውም እንደ ሰንፌር ነበር። ח ኼት ח ኼት 8 አሁን ግን ከጥላሸት ይልቅ ጠቍረዋል፤ በመንገድም የሚያውቃቸው የለም፤ ቈዳቸው ከዐጥንታቸው ጋራ ተጣብቋል፤ እንደ ዕንጨትም ደርቀዋል። ט ቴት ט ቴት 9 በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣ በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤ ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣ በራብ ደርቀው ያልቃሉ። י ዮድ י ዮድ 10 ሕዝቤ ባለቀበት ጊዜ፣ ምግብ እንዲሆኗቸው፣ ርኅሩኆቹ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው፣ ልጆቻቸውን ቀቀሉ። כ ካፍ כ ካፍ 11 እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤ ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤ መሠረቷን እንዲበላ፣ በጽዮን እሳት ለኰሰ። ל ላሜድ ל ላሜድ 12 ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣ የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣ የምድር ነገሥታት፣ ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም። מ ሜም מ ሜም 13 ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣ ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኗል፤ በውስጧ፣ የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና። נ ኑን נ ኑን 14 እንደ ታወሩ ሰዎች፣ በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤ ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣ በደም እጅግ ረክሰዋል። ס ሳሜክ ס ሳሜክ 15 ሰዎች “ሂዱ! እናንተ ርኩሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤ “ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤ ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣ በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣ “ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ። ע ዐዪን ע ዐዪን 16 እግዚአብሔር ራሱ በትኗቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤ ካህናቱ አልተከበሩም፤ ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም። פ ፌ פ ፌ 17 ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣ ዐይኖቻችን ደከሙ፤ ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣ ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን። צ ጻዲ צ ጻዲ 18 ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤ ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤ መጨረሻችን ቀርቧል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤ ፍጻሜያችን መጥቷልና። ק ቆፍ ק ቆፍ 19 ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣ ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በምድረ በዳም ሸመቁብን። ר ሬሽ ר ሬሽ 20 በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣ በወጥመዳቸው ተያዘ፤ በጥላው ሥር፣ በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር። ש ሲን እና ሺን ש ሲን እና ሺን 21 አንቺ በዖፅ ምድር የምትኖሪ፣ የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ ነገር ግን ለአንቺም ደግሞ ጽዋው ይደርስሻል፤ ትሰክሪያለሽ፤ ዕርቃንሽንም ትጋለጫለሽ። ת ታው ת ታው 22 የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ቅጣትሽ ያበቃል፤ እርሱም የስደትሽን ዘመን አያራዝምም፤ ነገር ግን አንቺ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፤ ኀጢአትሽን ይቀጣል፤ ክፋትሽንም ይፋ ያወጣል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.