Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሰቈቃወ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


א አሌፍ
א አሌፍ

1 በቍጣው በትር፣ መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ።

2 ከፊቱ አስወጣኝ፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ እንድሄድ አደረገኝ።

3 በርግጥ ቀኑን ሁሉ በመደጋገም፣ እጁን በላዬ ላይ መለሰ።


ב ቤት
ב ቤት

4 እርሱ ሥጋዬንና ቈዳዬን አስረጀ፤ ዐጥንቶቼንም ሰባበረ።

5 በምሬትና በድካም፣ ቅጥር ሠራብኝ፤ ዙሪያዬንም ከበበኝ።

6 ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደ ሆናቸው፣ በጨለማ እንድኖር አደረገኝ።


ג ጊሜል
ג ጊሜል

7 በቅጥር ውስጥ ዘጋብኝ፤ ስለዚህ ማምለጥ አልቻልሁም፤ የእስር ሰንሰለቴንም አከበደብኝ።

8 ርዳታ ፈልጌ ብጣራና ብጮኽ እንኳ፣ ጸሎቴን መስማት አልፈለገም።

9 መንገዴን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ ጐዳናዬንም አጣመመ።


ד ዳሌት
ד ዳሌት

10 አሸምቆ እንደ ተኛ ድብ፣ እንደ አደባም አንበሳ፣

11 ከመንገድ ጐትቶ አስወጣኝ፤ ቈራረጠኝም፤ ያለ ረዳትም ተወኝ።

12 ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻዎቹም ዒላማ አደረገኝ።


ה ሄ
ה ሄ

13 ፍላጻዎችን ከሰገባው አውጥቶ፣ ልቤን ወጋው።

14 ለሕዝቤ ሁሉ ማላገጫ ሆንሁኝ፤ ቀኑን ሙሉ በመሣለቅ ያዜሙብኛል።

15 መራራ ሥር አበላኝ፤ ሐሞትም አጠገበኝ።


ו ዋው
ו ዋው

16 ጥርሴን በድንጋይ ሰበረ፤ በትቢያ ውስጥ ረጋገጠኝ።

17 ነፍሴ ሰላምን ዐጣች፤ ደስታ ምን እንደ ሆነ ረሳሁ።

18 ስለዚህ፣ “ክብሬ፣ ከእግዚአብሔርም ተስፋ ያደረግሁት ሁሉ ሄዷል” አልሁ።


ז ዛይን
ז ዛይን

19 የጭንቀቴንና የመንከራተቴን፣ ምሬትንና ሐሞትን ዐስባለሁ።

20 ዘወትር አስበዋለሁ፤ ነፍሴም በውስጤ ተዋርዳለች።

21 ሆኖም ይህን ዐስባለሁ፤ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤


ח ኼት
ח ኼት

22 ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።

23 ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው።

24 ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።”


ט ቴት
ט ቴት

25 እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው።

26 ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።

27 ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው።


י ዮድ
י ዮድ

28 ብቻውን ዝም ብሎ ይቀመጥ፤ እግዚአብሔር አሸክሞታልና።

29 ፊቱን በዐቧራ ውስጥ ይቅበር፤ ተስፋ ሊኖር ይችላልና።

30 ጕንጩን ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ውርደትንም ይጥገብ።


כ ካፍ
כ ካፍ

31 ጌታ ሰውን፣ ለዘላለም አይጥልምና፤

32 መከራን ቢያመጣ እንኳ ይራራል፤ ታላቅ ፍቅሩ አይለወጥምና።

33 ሆነ ብሎ ችግርን፣ ወይም መከራን በሰው ልጆች ላይ አያመጣምና።


ל ላሜድ
ל ላሜድ

34 የምድሪቱ እስረኞች ሁሉ፣ በእግር ሲረገጡ፣

35 በልዑል ፊት፣ ሰው መብቱ ሲነፈገው፣

36 ሰው ፍትሕ ሲጓደልበት፣ ጌታ እንዲህ ዐይነቱን ነገር አያይምን?


מ ሜም
מ ሜም

37 ጌታ ካላዘዘ በቀር፣ ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው?

38 ክፉም ሆነ መልካም ነገር፣ ከልዑል አፍ የሚወጣ አይደለምን?

39 ታዲያ ሕያው ሰው በኀጢአቱ ሲቀጣ፣ ስለ ምን ያጕረመርማል?


נ ኑን
נ ኑን

40 መንገዳችንን እንመርምር፤ እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።

41 ልባችንን ከእጃችን ጋራ በሰማይ ወዳለው ወደ አምላካችን እናንሣ፤ እንዲህም እንበል፤

42 “ዐምፀናል፤ ኀጢአትም ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልኸንም።


ס ሳሜክ
ס ሳሜክ

43 “ራስህን በቍጣ ከደንህ፤ አሳደድኸንም፤ ያለ ርኅራኄም ገደልኸን።

44 ጸሎት እንዳያልፍ፣ ራስህን በደመና ሸፈንህ።

45 በአሕዛብ መካከል፣ አተላና ጥራጊ አደረግኸን።


ע ዐዪን
ע ዐዪን

46 “ጠላቶቻችን ሁሉ፣ አፋቸውን በእኛ ላይ ከፈቱ።

47 በጥፋትና በመፈራረስ፣ በችግርና በሽብር ተሠቃየን።”

48 የእንባ ጐርፍ ከዐይኔ ፈሰሰ፤ ሕዝቤ ዐልቋልና።


פ ፌ
פ ፌ

49 ያለ ዕረፍት፣ ያለ ማቋረጥ ዐይኖቼ እንባ ያፈስሳሉ፤

50 እግዚአብሔር ከላይ፣ ከሰማይ እስኪያይ ድረስ።

51 በከተማዬ ባሉት ሴቶች ሁሉ ላይ የደረሰውን ማየቴ፣ ነፍሴን አስጨነቃት።


צ ጻዲ
צ ጻዲ

52 ያለ ምክንያት ጠላቶቼ የሆኑ፣ እንደ ወፍ ዐደኑኝ።

53 ሕይወቴን በጕድጓድ ውስጥ ሊያጠፉ ሞከሩ፣ ድንጋይም በላዬ አደረጉ።

54 ውሃ ሞልቶ በዐናቴ ላይ ፈሰሰ፤ ጠፍቻለሁ ብዬ አሰብሁ።


ק ቆፍ
ק ቆፍ

55 በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ሳለሁ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተን ስም ጠራሁ።

56 ልመናዬን ሰምተሃል፤ “ርዳታም ፈልጌ ስጮኽ፣ ከመስማት ጆሮህን አትከልክል።”

57 በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ “አትፍራ” አልኸኝ።


ר ሬሽ
ר ሬሽ

58 ጌታ ሆይ፤ ለእኔ ተሟገትኽልኝ፤ ሕይወቴንም ተቤዠህ።

59 እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኔ ላይ የተደረገውን ግፍ አየህ፤ ፍርዴን ፍረድልኝ!

60 በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሰቡትን ዐድማ አየህ።


ש ሲን እና ሺን
ש ሲን እና ሺን

61 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስድባቸውን ሁሉ፣ በእኔ ላይ ያሰቡትን ዐድማ ሁሉ ሰማህ፤

62 ይህም ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ፣ ጠላቶቼ የሚያውጠነጥኑትና የሚያንሾካሹኩት ነው።

63 ተመልከታቸው! ቆመውም ሆነ ተቀምጠው፣ በዘፈናቸው ይሣለቁብኛል።


ת ታው
ת ታው

64 እግዚአብሔር ሆይ፤ እጆቻቸው ላደረጉት፣ የሚገባውን መልሰህ ክፈላቸው።

65 በልባቸው ላይ መጋረጃን ዘርጋ፤ ርግማንህም በላያቸው ይሁን!

66 ከእግዚአብሔር ሰማያት በታች፣ በቍጣህ አሳድዳቸው፤ አጥፋቸውም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告