ሰቈቃወ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምא አሌፍ א አሌፍ 1 ጌታ የጽዮንን ሴት ልጅ፣ በቍጣው ደመና እንዴት ጋረዳት! ከሰማይ ወደ ምድር፣ የእስራኤልን ክብር ወርውሮ ጣለው፤ በቍጣው ቀን፣ የእግሩን መቀመጫ አላስታወሰም። ב ቤት ב ቤት 2 የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ፣ ጌታ ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤ የይሁዳን ሴት ልጅ ምሽጎች፣ በቍጣው አፈረሳቸው፤ መንግሥቷንና መሳፍንቷን፣ በማዋረድ ወደ ምድር ጣላቸው። ג ጊሜል ג ጊሜል 3 በጽኑ ቍጣው፣ የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ሰበረ፤ ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣ ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤ በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣ በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ። ד ዳሌት ד ዳሌት 4 እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤ ቀኝ እጁ ተዘጋጅታለች፤ ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤ እንደ ጠላት ዐረዳቸው፤ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ላይ፣ ቍጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ። ה ሄ ה ሄ 5 ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፤ እስራኤልንም ዋጠ፤ ቤተ መንግሥቶቿን ሁሉ ዋጠ፤ ምሽጎቿን አፈራረሰ፤ በይሁዳ ሴት ልጅ፣ ልቅሶንና ሰቈቃን አበዛ። ו ዋው ו ዋው 6 ማደሪያውን እንደ አትክልት ስፍራ ባዶ አደረገ፤ መሰብሰቢያ ስፍራውን አፈረሰ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን፣ ዓመት በዓላቶቿንና ሰንበታቷን እንድትረሳ አደረጋት፤ በጽኑ ቍጣው፣ ንጉሡንና ካህኑን እጅግ ናቀ። ז ዛይን ז ዛይን 7 ጌታ መሠዊያውን ናቀ፤ መቅደሱንም ተወ፤ የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣ ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤ በዓመት በዓል ቀን እንደሚደረገው በእግዚአብሔር ቤት በኀይል ጮኹ። ח ኼት ח ኼት 8 በጽዮን ሴት ልጅ ዙሪያ ያለውን ቅጥር፣ እግዚአብሔር ለማፍረስ ወሰነ፤ የመለኪያ ገመድ ዘረጋ፤ ከማጥፋትም እጆቹን አልሰበሰበም፤ ምሽጎችና ቅጥሮች እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነትም ጠፉ። ט ቴት ט ቴት 9 በሮቿ ወደ ምድር ሰመጡ፤ የብረት መወርወሪያዎቻቸውን ሰባበረ፤ አጠፋቸውም፤ ንጉሧና መሳፍንቷ በአሕዛብ መካከል ተማርከው ተሰድደዋል፤ ሕጉ ከእንግዲህ አይኖርም፤ ነቢያቷም ከእንግዲህ፣ ከእግዚአብሔር ራእይ አያገኙም። י ዮድ י ዮድ 10 የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች፣ በምድር ላይ በዝምታ ተቀምጠዋል፤ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤ ማቅም ለበሱ፤ የኢየሩሳሌም ወጣት ሴቶች፣ ራሳቸውን ወደ ምድር ዝቅ አደረጉ። כ ካፍ כ ካፍ 11 ዐይኔ በልቅሶ ደከመ፤ ነፍሴ በውስጤ ተሠቃየች፤ ልቤም በሐዘን ፈሰሰች፣ በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣ ሕዝቤ ተደምስሰዋልና፤ ልጆችና ሕፃናት ደክመዋልና። ל ላሜድ ל ላሜድ 12 በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣ እንደ ቈሰሉ ሰዎች ሲደክሙ፣ በእናታቸው ክንድ ላይ፣ ነፍሳቸው በመውጣት ላይ ሳለች፣ “ምግብና የወይን ጠጅ የት አለ?” እያሉ እናቶቻቸውን ይጠይቃሉ። מ ሜም מ ሜም 13 የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፤ ስላንቺ ምን ማለት እችላለሁ? ከምንስ ጋራ አወዳድርሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አጽናናሽ ዘንድ፣ በምን ልመስልሽ እችላለሁ? ቍስልሽ እንደ ባሕር ጥልቅ ነው፤ ማንስ ሊፈውስሽ ይችላል? נ ኑን נ ኑን 14 የነቢያቶችሽ ራእይ፣ ሐሰትና ከንቱ ነው፤ ምርኮኛነትሽን ለማስቀረት፣ ኀጢአትሽን አይገልጡም። የሚሰጡሽም የትንቢት ቃል፣ የሚያሳስትና ከመንገድ የሚያወጣ ነው። ס ሳሜክ ס ሳሜክ 15 በአጠገብሽ የሚያልፉ ሁሉ፣ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻል፤ “የውበት መደምደሚያ፣ የምድር ሁሉ ደስታ፣ የተባለች ከተማ ይህች ናትን?” እያሉ ራሳቸውን በመነቅነቅ፣ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያሾፋሉ። ע ዐዪን ע ዐዪን 16 ጠላቶችሽ ሁሉ በአንድ ላይ፣ አፋቸውን በኀይል ከፈቱ፤ ጥርሳቸውን እያፏጩ አሾፉ፤ እንዲህም አሉ፤ “ውጠናታል፤ የናፈቅነው ጊዜ ይህ ነበር፤ ኖረንም ልናየው በቃን።” פ ፌ פ ፌ 17 እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ ከረዥም ጊዜ በፊት የተናገረውን፣ ቃሉን ፈጸመ፤ ያለ ርኅራኄ አፈረሰሽ፤ ጠላት በሥቃይሽ ላይ እንዲደሰት፣ የጠላትሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ። צ ጻዲ צ ጻዲ 18 የሕዝቡ ልብ፣ ወደ ጌታ ጮኸ። የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፤ ቀንና ሌሊት፣ እንባሽ እንደ ወንዝ ይፍሰስ፤ ለራስሽ ዕረፍትን አትስጪ፣ ዐይኖችሽ ከማንባት አያቋርጡ። ק ቆፍ ק ቆፍ 19 የሌሊቱ ሰዓት ሲጀምር፣ ተነሺ በሌሊት ጩኺ፤ በጌታ ፊት፣ ልብሽን እንደ ውሃ አፍስሺ፤ በየመንገዱ ዳር ላይ፣ በራብ ስለ ወደቁት፣ ስለ ልጆችሽ ሕይወት፣ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ። ר ሬሽ ר ሬሽ 20 “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እይ፤ ተመልከትም፤ በማን ላይ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ? በውኑ እናቶች ሕፃኖቻቸውን፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆች ይብሉን? ካህኑና ነቢዩስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን? ש ሲን እና ሺን ש ሲን እና ሺን 21 “በየመንገዱ ዐቧራ ላይ፣ ወጣትና ሽማግሌ በአንድነት ወደቁ፤ ወይዛዝርቴና ጐበዛዝቴ፣ በሰይፍ ተገደሉ፤ በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ ያለ ርኅራኄም ዐረድሃቸው። ת ታው ת ታው 22 “በበዓል ቀን ለግብዣ እንደምትጠራ፣ ሽብርን ከየአቅጣጫው በእኔ ላይ ጠራህ፤ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ማንም አላመለጠም ወይም አልተረፈም፤ የተንከባከብኋቸውንና ያሳደግኋቸውን፣ ጠላቴ አጠፋብኝ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.