መሳፍንት 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምአቤሜሌክ 1 የይሩባኣል ልጅ አቢሜሌክ ወደ እናቱ ወንድሞች ወደ ሴኬም ሄደ። እነርሱንና የእናቱን ጐሣዎች በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ 2 “የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቍራጭ፣ የዐጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።” 3 የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ገዦች በሙሉ ነገሩ፤ አቢሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል” ብለዋልና። 4 እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል ብር ሰጡት፤ አቢሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት። 5 ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩባኣልን ልጆች፣ ወንድሞቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩባኣል የመጨረሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ። 6 የሴኬምና የቤት ሚሎ ገዦች በሙሉ አቢሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ። 7 ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ “የሴኬም ገዦች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ። 8 ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት። 9 “የወይራ ዛፍም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?’ አለ። 10 “ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት። 11 “በለስ ግን፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?’ አለ። 12 “ከዚያም ዛፎቹ የወይን ተክልን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት። 13 “የወይን ተክሉም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ አማልክትንና ሰዎችን ደስ የሚያሠኘውን የወይን ጠጄን መስጠት ልተውን?’ አለ። 14 “በመጨረሻም ዛፎቹ በሙሉ የእሾኽ ቍጥቋጦን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት። 15 “የእሾኽ ቍጥቋጦውም ዛፎቹን፣ ‘በርግጥ ቀብታችሁ በላያችሁ የምታነግሡኝ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ግን እሳት ከእሾኽ ቍጥቋጦው ይነሣ፤ የሊባኖስንም ዝግባዎች ይብላ!’ አላቸው። 16 “እንግዲህ አቢሜሌክን ስታነግሡት በእውነትና ያለ እንከን አድርጋችሁት ከሆነ፣ ይሩባኣልንና ቤተ ሰቡን በበጎ ዐይን ተመልክታችሁ ላደረገው የሚገባውን አይታችሁለት ከሆነ፣ 17 አባቴ ለእናንተ መዋጋቱን፣ ከምድያማውያን እጅ ሊያድናችሁ ሕይወቱን መስጠቱን ዐሰባችሁ ማለት ነው። 18 ነገር ግን እናንተ ዛሬ በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ዐመፃችሁ፤ ሰባ ልጆቹን በአንዲት ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ዘመዳችሁ ስለ ሆነም አባቴ ከባሪያው የወለደውን ልጅ አቢሜሌክን በሴኬም ገዦች ላይ አነገሣችሁት። 19 እንግዲህ ዛሬ በይሩባኣልና በቤተ ሰቡ ላይ ያደረጋችሁት በእውነትና ያለ እንከን ከሆነ እናንተ በአቢሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው! 20 ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቢሜሌክ ትውጣና እናንተን፣ የሴኬምንና የቤት ሚሎን ነዋሪዎች ትብላ፤ እንዲሁም እሳት ከእናንተ፣ ከሴኬምና ከቤት ሚሎን ገዦች ትውጣና አቢሜሌክን ትብላ።” 21 ከዚህ በኋላ ኢዮአታም ሸሽቶ አመለጠ፤ ብኤር ወደ ተባለች ቦታም መጣ፤ ወንድሙንም አቢሜሌክን ፈርቶ ስለ ነበር እዚያው ይኖር ጀመር። 22 አቢሜሌክ እስራኤልን ሦስት ዓመት ከገዛ በኋላ፣ 23 እግዚአብሔር በአቢሜሌክና በሴኬም ገዦች መካከል ክፉ መንፈስ ሰደደ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች አቢሜሌክን ከዱት። 24 ይህን ያደረገውም፣ በሰባው የይሩባኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፣ ወንድማቸውን አቢሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ገዦች ለመበቀል ነው። 25 የሴኬም ገዦችም አቢሜሌክን ሸምቀው የሚጠባበቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቢሜሌክ ደረሰው። 26 በዚህ ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋራ ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ገዦች ተማመኑበት። 27 ወደ ዕርሻ ወጥተው ወይናቸውን ለቅመው ከጨመቁ በኋላ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አቢሜሌክን ሰደቡ። 28 የአቤድ ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፤ “እንገዛለት ዘንድ አቢሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድን ናት? እርሱ የይሩባኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የርሱ ረዳት ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ ለምን ለአቢሜሌክ እንገዛለን? 29 ምነው ይህን ሕዝብ የማዝዘው እኔ በሆንሁ ኖሮ! አቢሜሌክን አስወግደው ነበር፤ ‘ሰራዊትህን አብዝተህ ውጣ!’ እለው ነበር።” 30 የከተማዪቱ ገዥ ዜቡል፣ የአቤድ ልጅ ገዓል ያለውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ 31 ወደ አቢሜሌክም መልእክተኞች በምስጢር ልኮ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተው ከተማዪቱ እንድትሸፍትብህ አድርገዋል። 32 ስለዚህ በሌሊት ሰዎችህን ይዘህ ወጥተህ ሜዳው ላይ ማድፈጥ አለብህ፤ 33 ጧት ፀሓይ ስትወጣም ወደ ከተማዪቱ ገሥግሥ፤ ገዓልና ሰዎቹ ሊገጥሙህ በሚወጡበት ጊዜ እጅህ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርግ።” 34 ስለዚህ አቢሜሌክና ሰዎቹ በሙሉ በሌሊት ወጡ፤ በአራት ምድብ ሆነውም በሴኬም አጠገብ አደፈጡ። 35 የአቤድ ልጅ ገዓል ከከተማዪቱ ወጥቶ በመግቢያው በር ላይ ሲቆም፣ አቢሜሌክና ሰዎቹ ካደፈጡበት ወጡ። 36 ገዓል ባያቸው ጊዜ ዜቡልን፣ “ተመልከት፤ ከተራራው ጫፍ ሕዝብ እየወረደ ነው” አለው። ዜቡልም መልሶ፣ “የተራሮች ጥላ ሰዎች መስሎ ተሳስተህ” ነው አለው። 37 ገዓልም፣ “ተመልከት እንጂ ሕዝብ እኮ ከተራራው ወገብ ላይ እየደረሰ ነው፤ አንዱ ክፍልም በቃላተኞች ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” ብሎ እንደ ገና ተናገረ። 38 ከዚያም ዜቡል፣ “እንገዛለት ዘንድ አቢሜሌክ ማን ነው? ብለህ የደነፋኸው አሁን የት አለ? ያቃለልሀቸውስ ሰዎች እነዚህ አይደሉምን? በል ውጣና ግጠማቸው” አለው። 39 ገዓል የሴኬምን ገዦች መርቶ በመውጣት አቢሜሌክን ተዋጋው፤ 40 ሆኖም አቢሜሌክ አሳደደው፤ እስከ መግቢያው በር ድረስ ባለው መንገድ ሲሸሹም ብዙ ሰዎች ቈስለው ወደቁ። 41 አቢሜሌክ በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው። 42 በማግስቱም የሴኬም ሕዝብ ወደ ዕርሻ ወጡ፤ ይህም ለአቢሜሌክ ተነገረው፤ 43 እርሱም ሰዎቹን አስከትሎ ወጣ፤ ከዚያም ሰዎቹን ሦስት ቦታ መድቦ በዕርሻዎቹ ውስጥ አድፍጠው እንዲጠባበቁ አደረገ። አቢሜሌክ የሴኬም ሰዎች ከከተማዪቱ መውጣታቸውን እንዳየም ካደፈጠበት ሊወጋቸው ተነሣ። 44 ከዚያም አቢሜሌክና ዐብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፣ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው። 45 በዚያ ዕለት አቢሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማዪቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማዪቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት። 46 በሴኬም ግንብ ውስጥ የሚኖሩ ገዦች ይህን እንደ ሰሙ፤ በኤልበሪት ቤተ መቅደስ ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገቡ። 47 አቢሜሌክም በሴኬም ግንብ ገዦች ሁሉ መመሸጋቸውን ሲሰማ፣ 48 እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቢሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውም ላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፣ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው። 49 ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቢሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ግንብ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺሕ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ። 50 ከዚያም አቢሜሌክ ወደ ቴቤስ በመሄድ ከተማዪቱን ከብቦ ያዛት። 51 ሆኖም በከተማዪቱ ውስጥ ብርቱ ግንብ ስለ ነበር፣ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ የከተማዪቱ ገዦችም ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በውስጥ ዘግተው ወደ ግንቡ ጣራ ወጡ። 52 አቢሜሌክም ተዋግቶ ግንቡን ያዘ፤ ይሁን እንጂ እሳት ለመለኰስ ወደ ግንቡ መግቢያ አጠገብ እንደ ደረሰ፣ 53 አንዲት ሴት ከላይ የወፍጮ መጅ በአቢሜሌክ ራስ ላይ ለቀቀችበት፤ ጭንቅላቱንም አፈረሰችው። 54 ወዲያውም ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፣ “ ‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉ እባክህ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ” አለው። ስለዚህ አገልጋዩ ወጋው፤ እርሱም ሞተ። 55 እስራኤላውያንም አቢሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ወደ የቤታቸው ተመለሱ። 56 አቢሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል፣ በአባቱ ላይ ስላደረሰው በደል እግዚአብሔር የእጁን ከፈለው። 57 በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰው፤ የይሩባኣል ልጅ የኢዮአታም ርግማን ደረሰባቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.