መሳፍንት 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየዲቦራ መዝሙር 1 በዚያ ዕለት ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ ይህን ቅኔ ተቀኙ፤ 2 “በእስራኤል ያሉ መሳፍንት ሲመሩ፣ ሕዝቡም በፈቃዱ ራሱን ሲያስገዛ፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ። 3 “እናንተ ነገሥታት ይህን ስሙ፤ ገዦችም አድምጡ፤ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ደግሜም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ። 4 “እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፣ ከኤዶም ምድርም በተነሣህ ጊዜ፣ ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ሰማያትም ዝናብ አዘነቡ፤ ደመናዎችም ውሃ አፈሰሱ። 5 ተራሮች በሲና አምላክ በእግዚአብሔር ፊት፣ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ተናወጡ። 6 “በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፣ በኢያዔል ጊዜ መንገዶች ባድማ ሆኑ፤ ተጓዦችም በጠመዝማዛ መንገድ ሄዱ። 7 ለእስራኤል እናት ሆኜ እኔ ዲቦራ እስክነሣ ድረስ በእስራኤል ያለው የከተማ ኑሮ አበቃለት፤ 8 አዳዲስ አማልክትን በተከተሉ ጊዜ፣ ጦርነት እስከ ከተማው በር መጣ፤ ጋሻም ሆነ ጦር፣ በአርባ ሺሕ እስራኤላውያን መካከል አልተገኘም። 9 ልቤ ከእስራኤል መሳፍንት፣ ፈቃደኞችም ከሆኑ ሰዎች ጋራ ነው፤ እግዚአብሔር ይመስገን። 10 “እናንተ በነጫጭ አህዮች የምትጋልቡ፣ በባለ ግላስ ኮርቻ ላይ የምትቀመጡ፣ በመንገድ ላይ የምትጓዙ፣ በውሃ ምንጮች ዙሪያ ያለውን፣ 11 የዝማሬ ድምፅ ስሙ። ይህም የእግዚአብሔር የጽድቅ ሥራ፣ ጦረኞቹም በእስራኤል ያደረጉትን ያስታውሳል። “ከዚያም የእግዚአብሔር ሕዝቦች፣ ወደ ከተማዪቱ በሮች ወረዱ። 12 ‘ዲቦራ ሆይ፤ ንቂ፤ ንቂ፤ ንቂ፤ ንቂ፤ ቅኔም ተቀኚ፤ የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ ሆይ፤ ተነሣ፤ ምርኮኞችህንም ማርከህ ውሰድ’ አሉ። 13 “የቀሩትም ሰዎች፣ ወደ መኳንንቱ ወረዱ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ እንደ ኀያል ጦረኛ ወደ እኔ መጣ። 14 መሠረታቸው ከአማሌቅ የሆነ አንዳንዶች ከኤፍሬም መጡ፤ ብንያም አንተን ከተከተሉ ሰዎች ጋራ ነበር፤ የጦር አዛዦች ከማኪር፣ የሥልጣን በትር የያዙም ከዛብሎን ወረዱ። 15 የይሳኮር መሳፍንት ከዲቦራ ጋራ ነበሩ፤ ይሳኮርም ራሱ ወደ ሸለቆው ከኋላው በመከተል፣ ከባርቅ ጋራ ነበረ። በሮቤል አውራጃዎች፣ ብዙ የልብ ምርምር ነበር። 16 በበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? መንጎችን የሚጠራውን ፉጨት ለመስማት ነውን? በሮቤል አውራጃዎች፣ ብዙ የልብ ምርምር ነበር። 17 ገለዓድ ከዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳን ለምን በመርከብ ውስጥ ዘገየ? አሴር በጠረፍ ቀረ፤ በባሕሩ ዳርቻም ተቀመጠ። 18 የዛብሎን ሰዎች ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ የንፍታሌም ሰዎች እንደዚሁ በምድሪቱ ኰረብቶች አደረጉ። 19 “ነገሥታት መጡ፤ ተዋጉም፤ የከነዓን ነገሥታት፣ በመጊዶ ውሆች አጠገብ በታዕናክ ተዋጉ፤ ብርም ሆነ ሌላ ምርኮ ተሸክመው አልሄዱም። 20 ከሰማያት ከዋክብት ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ሲሣራን ገጠሙት። 21 ጥንታዊው ወንዝ፣ የቂሶን ወንዝ፣ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው፤ ነፍሴ ሆይ፤ በኀይል ገሥግሺ 22 የፈረሶች ኰቴ ድምፅ በኀይል ተሰማ፤ ጋለቡ፤ በኀይልም ፈጥነው ጋለቡ። 23 የእግዚአብሔር መልአክ፣ ‘ሜሮዝን ርገሙ፤’ ‘ሕዝቧንም ዐብራችሁ ርገሙ፤ ከኀያላን ሰልፍ እግዚአብሔርን ለመርዳት፣ በእግዚአብሔርም ጐን ለመቆም አልመጡምና’ አለ። 24 “የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል፣ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶች ሁሉ የተባረከች ትሁን። 25 ውሃ ለመነ፤ ወተት ሰጠችው፤ ለመኳንንት በሚገባ ዕቃ፣ ርጎ አቀረበችለት። 26 እጇ ካስማ ያዘ፤ ቀኝ እጇም የሠራተኛ መዶሻ ጨበጠ፤ ሲሣራን መታችው፤ ራሱንም ተረከከችው፤ ክፉኛ ወጋችው፤ ጆሮ ግንዱን በሳችው። 27 በእግሯ ሥር ተደፋ፤ ወደቀ፤ በዚያም ተዘረረ፤ በእግሯ ሥር ተደፋ፤ ወደቀ፤ በተደፋበት በዚያ ወደቀ፤ ሞተም። 28 “የሲሣራ እናት በመስኮት ተመለከተች፤ በዐይነ ርግቡ ቀዳዳም ጮኻ ተጣራች፤ ‘ለምን ሠረገላው ሳይመጣ ዘገየ? የሠረገሎቹስ ድምፅ ለምን ጠፋ?’ አለች። 29 ብልኀተኞች ወይዛዝርቷም መለሱላት፤ እርሷ ግን ለራሷ እንዲህ አለች፤ 30 ‘ምርኮ አግኝተው እየተከፋፈሉ፣ እያንዳንዱም ሰው አንዲት ወይም ሁለት ልጃገረዶች እየወሰደ አይደለምን? ይህ ሁሉ ምርኮ፣ በቀለም ያጌጡ ልብሶች ለሲሣራ ደርሰውት፣ በጌጣጌጥ የተጠለፉ ልብሶች ለዐንገቴ ይዞልኝ እየመጣ አይደለምን?’ 31 “እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፤ አንተን የሚወድዱህ ግን፣ የንጋት ፀሓይ በኀይል እንደሚወጣ እንዲያ ይሁኑ።” ከዚያም በኋላ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.