መሳፍንት 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምዲቦራ 1 ናዖድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ። 2 ስለዚህም እግዚአብሔር በአሦር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነዓን ንጉሥ ለኢያቢስ አሳልፎ ሸጣቸው። የኢያቢስ ሰራዊት አዛዥ፣ በአሪሶት ሐጎይም የሚኖረው ሲሣራ ነበረ፤ 3 እርሱም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩት እስራኤላውያንን ሃያ ዓመት እጅግ አስጨነቃቸው፤ እነርሱም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 4 በዚያ ጊዜ የለፊዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበረች። 5 እርሷም በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፣ በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እርሷ ይመጡ ነበር። 6 ዲቦራ፣ በንፍታሌም ውስጥ ቃዴስ በተባለች ከተማ ይኖር የነበረውን የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ያዝሃል፤ ‘ተነሣ፤ ከንፍታሌምና ከዛብሎን ዐሥር ሺሕ ሰዎች ይዘህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፤ 7 እኔም የኢያቢስን ሰራዊት አዛዥ ሲሣራን ከሠረገሎቹና ከሰራዊቱ ጋራ ቂሶን ወንዝ እንዲመጣ አነሣሣዋለሁ፤ በእጅህም አሳልፌ እሰጥሃለሁ።’ ” 8 ባርቅም፣ “ዐብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ፤ ዐብረሽኝ የማትሄጂ ከሆነ ግን አልሄድም” አላት። 9 ዲቦራ መልሳ፣ “ይሁን ዕሺ፤ መሄዱን ዐብሬህ እሄዳለሁ፤ በዚህ ሁኔታ የምትሄድ ከሆነ ግን ክብሩ ለአንተ አይሆንም፤ እግዚአብሔር ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ይሰጣልና” አለችው። ስለዚህ ዲቦራ ከባርቅ ጋራ ወደ ቃዴስ ሄደች፤ 10 በዚያም ባርቅ የዛብሎንንና የንፍታሌምን ሰዎች ወደ ቃዴስ ጠራቸው፤ ዐሥር ሺሕ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም ዐብራው ሄደች። 11 በዚያ ጊዜ ቄናዊው ሔቤር፣ የሙሴ ዐማች የኦባብ ልጆች ከሆኑት ከሌሎቹ ቄናውያን ተለይቶ በቃዴስ አጠገብ ጻዕናይም ከተባለ ቦታ ከሚገኘው ትልቅ ወርካ ጥግ ድንኳኑን ተክሎ ነበር። 12 የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱን ሲሣራ በሰማ ጊዜ፣ 13 ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከአሪሶት ሐጎይም እስከ ቂሶን ወንዝ ያለውን ሰራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ። 14 በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባርቅን፣ “ተነሣ! እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሰጠባት ቀን ይህች ናት፤ እነሆ እግዚአብሔር በፊትህ ቀድሞ ወጥቷል” አለችው። ስለዚህ ባራቅ ዐሥር ሺሕ ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ። 15 እግዚአብሔር ሲሣራንና ሠረገሎቹን ሁሉ በባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት እጅግ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ። 16 ባርቅ ግን የሲሣራን ሠረገሎችና ሰራዊቱን እስከ አሪሶት ሐጎይም ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራ ሰራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። 17 በአሦር ንጉሥ በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ጐሣ መካከል መልካም ግንኙነት ስለ ነበር ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሮጠ። 18 ኢያዔልም ወጥታ ሲሣራን ተቀበለችውና፣ “ጌታዬ፤ ወደ ውስጥ ግባ፤ ፈጽሞ አትፍራ” አለችው፤ ሲሣራም ወደ ድንኳኗ ገባ፤ እርሷም በልብስ ሸፍና ደበቀችው። 19 ሲሣራም፣ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ዕቃውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደ ገናም ሸፈነችው። 20 እርሱም፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፣ ‘እዚህ ሰው አለ?’ ቢልሽ፣ ‘የለም’ በይ” አላት። 21 የሔቤር ሚስት ኢያዔል ግን ሲሣራ ደክሞ፣ ከባድ እንቅልፍም ወስዶት ሳለ፣ የድንኳን ካስማና መዶሻ ይዛ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ከዚያም ካስማውን በመዶሻ ጆሮ ግንዱ ላይ መትታ ከመሬት ጋራ ሰፋችው፤ እርሱም ሞተ። 22 ባርቅ ሲሣራን በመከታተል ላይ ስለ ነበር ከዚያ ሲደርስ፣ ኢያዔል ከድንኳኗ ወጥታ “ና፤ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፤ ስለዚህ ከርሷ ጋራ ወደ ድንኳኗ ገባ፤ ሲሣራም በጆሮ ግንዱ ላይ ካስማ እንደ ተመታበት ሞቶ ተዘርሮ ነበረ። 23 በዚያች ዕለት እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤላውያን ፊት እንዲሸነፍ አደረገው፤ 24 ከነዓናዊውን ንጉሥ ኢያቢስን እስኪደመስሱ ድረስ የእስራኤላውያን ክንድ እየበረታ ሄደ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.