መሳፍንት 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእስራኤላውያን ከብንያማውያን ጋራ ተዋጉ 1 ከዚያም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እንዲሁም በገለዓድ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፤ በምጽጳም በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ። 2 የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች ሁሉ ቍጥራቸው አራት መቶ ሺሕ በሚሆን፣ ሰይፍ በሚመዝዙ እግረኞች ወታደሮች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ መካከል ተገኙ። 3 በዚህ ጊዜ ብንያማውያን፣ እስራኤላውያን ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ፤ ከዚያም እስራኤላውያን፣ “ይህ ክፉ ድርጊት እንዴት እንደ ተፈጸመ እስኪ ንገሩን?” ተባባሉ። 4 ስለዚህ የተገደለችው ሴት ባል ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና ቁባቴ በዚያ ለማደር በብንያም ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ መጣን። 5 የጊብዓም ገዦች በሌሊት ሊገድሉኝ ያደርኩበትን ቤት ከበቡት፤ ከዚያም በቁባቴ ላይ ስለ አመነዘሩባት ሞተች። 6 የቁባቴንም ሬሳ ከቈራረጥሁ በኋላ እያንዳንዱን ቍራጭ፣ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ወዳለበት አገር ሰደድሁ፤ ይህን ያደረግሁትም ሰዎቹ በእስራኤል ዘንድ አሠቃቂና አስነዋሪ ድርጊት ስለ ፈጸሙ ነው። 7 አሁንም እናንተ እስራኤላውያን ሁሉ በጕዳዩ ላይ ተወያዩበት፤ ፍርዳችሁንም ስጡ።” 8 ከዚያም ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመነሣት እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም፤ ማንኛችንም ወደ ቤታችን አንመለስም። 9 ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፤ በዕጣው መሠረት እንዘምትበታለን። 10 ከመላው የእስራኤል ነገዶችም ለሰራዊቱ ስንቅ እንዲይዙ፣ ከመቶው ዐሥር፣ ከሺው አንድ መቶ፣ ከዐሥር ሺሑ ደግሞ አንድ ሺሕ ሰው እንወስዳለን። ከዚያም ሰራዊቱ በብንያም ወደምትገኘው ጌባዕ በሚደርስበት ጊዜ፣ ነዋሪዎቿ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።” 11 ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመተባበር በከተማዪቱ ላይ ዘመቱባት። 12 የእስራኤል ነገዶች ለመላው የብንያም ነገድ እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላኩ፣ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ክፉ ድርጊት ምንድን ነው? 13 አሁንም እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ድርጊት ከእስራኤል እንድናስወግድ፣ እነዚያን የጊብዓን ምናምንቴ ሰዎች አሳልፋችሁ ስጡን።” ብንያማውያን ግን ወገኖቻቸውን እስራኤላውያንን አልሰሟቸውም ነበር፤ 14 ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ። 15 ብንያማውያንም ከመላው የጊብዓ ነዋሪዎች መካከል ከተመረጡት ሰባት መቶ ሰዎች ሌላ፣ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰዎች በአንድ አፍታ ከየከተሞቻቸው በተጨማሪ አሰባሰቡ። 16 በእነዚህም ሁሉ መካከል እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጕር እንኳ የማይስቱ ሰባት መቶ ምርጥ ግራኞች ነበሩ። 17 እስራኤላውያን፣ ብንያማውያንን ሳይጨምር፣ ሰይፍ የታጠቁ አራት መቶ ሺሕ ተዋጊዎች አሰባሰቡ። 18 እስራኤላውያን ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርም፣ “ብንያማውያንን ለመውጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ብሎ መለሰ። 19 በማግስቱም ጧት እስራኤላውያን ተነሥተው በጊብዓ አጠገብ ሰፈሩ፤ 20 የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 21 ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺሕ ሰዎች ገደሉ። 22 ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደ ገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 23 እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመግጠም እንደ ገና እንውጣን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ውጡና ግጠሟቸው” ብሎ መለሰላቸው። 24 በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ። 25 በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፣ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደ ገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ሰዎች ገደሉ። 26 የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያ ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ። 27 እስራኤላውያንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቁ፤ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት እዚያው ነበር፤ 28 የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በፊቱ ይቆም ነበር። እስራኤላውያንም፣ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደ ገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” ሲሉ ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “ሂዱ፤ በነገው ዕለት በእጃችሁ እሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። 29 ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ ድብቅ ጦር አኖሩ። 30 በሦስተኛውም ቀን ብንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 31 ብንያማውያንም ሊገጥሟቸው ወጡ፤ ከከተማዪቱም ርቀው እንዲሄዱ ተደረጉ፤ እንደ በፊቱም እስራኤላውያንን ይገድሉ ጀመር። ከዚህ የተነሣም በሜዳው እንዲሁም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስደው መንገዶች ላይ ሠላሳ ያህል ሰዎች ወድቀው ነበር። 32 ብንያማውያኑ፣ “እንደ በፊቱ ይኸው ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ፣ እስራኤላውያንም በበኩላቸው፣ “ወደ ኋላ እያፈገፈግን ከከተማዪቱ ወደ መንገዶቹ እንዲርቁ እናድርጋቸው” ይሉ ነበር። 33 የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጌባዕ በስተ ምዕራብ ካለው ቦታ ወጣ። 34 ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺሕ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፣ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር። 35 እግዚአብሔር ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ዐምስት ሺሕ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ። 36 ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለ ተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ። 37 ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሠራጭተውም መላዪቱን ከተማ በሰይፍ መቱ። 38 የእስራኤል ሰዎች ያሸመቀው ጦር በከተማዪቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳይ፣ 39 እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ተስማሙ። ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፣ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፣ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ። 40 ነገር ግን የጢሱ ዐምድ ከከተማዪቱ መነሣት በጀመረ ጊዜ፣ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ዞረው የመላዪቱ ከተማ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ። 41 ከዚያም እስራኤላውያን ዞረው አጠቋቸው፤ በዚህ ጊዜ ብንያማውያን ጥፋት እንደ ደረሰባቸው ስላወቁ እጅግ ደነገጡ። 42 ስለዚህም ጀርባቸውን አዙረው ከእስራኤላውያን ፊት ወደ ምድረ በዳው ሸሹ፤ ሆኖም ከጦርነት ማምለጥ አልቻሉም፤ ከየከተሞቹ የወጡ እስራኤላውያንም በዚያው ገደሏቸው። 43 ብንያማውያንንም ከበቧቸው፤ አሳደዷቸው፤ ከጊብዓ በስተምሥራቅ ትይዩ ባለውም ስፍራ በቀላሉ አሸነፏቸው፤ 44 በጦርነቱም ላይ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ብንያማውያን ወደቁ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ። 45 ብንያማውያን ጀርባቸውን አዙረው በምድረ በዳው በኩል ወደ ሬሞን ዐለት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እስራኤላውያን በመንገድ ላይ ዐምስት ሺሕ ሰው ገደሉባቸው፤ እስከ ጊድአምም ድረስ ተከታትለው ሁለት ሺሕ ሰዎች በተጨማሪ ገደሉ። 46 በዚያች ዕለት ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ዐምስት ሺሕ ብንያማውያን በጦር ሜዳ ወደቁ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ። 47 ነገር ግን ስድስት መቶ ሰዎች ጀርባቸውን አዙረው በምድረ በዳው ውስጥ ወዳለው ወደ ሬሞን ዐለት ሸሹ፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጡ። 48 ከዚያም እስራኤላውያን ወደ ብንያም ምድር ተመልሰው ከተሞቻቸውን በሙሉ እንዲሁም እንስሳቱንና በዚያ ያገኙትን ሁሉ በሰይፍ መቱ፤ በመንገዳቸው ያገኙትን ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.