መሳፍንት 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየእግዚአብሔር መልአክ በቦኪም 1 የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ‘ከእናንተ ጋራ የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ 2 እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋራ ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤’ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድን ነው? 3 ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፣ አማልክታቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” 4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ በተናገረ ጊዜ፣ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 5 ያን ስፍራ ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ያለ መታዘዝ ውጤት 6 ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ። 7 ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ። 8 የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። 9 እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በተምናሔሬስ ቀበሩት። 10 ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። 11 ከዚያም እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። 12 ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም። እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤ 13 እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አምልከዋልና 14 እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው። 15 እስራኤላውያን ለውጊያ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረውና እንደ ማለው ይሸነፉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ ተጨነቁ። 16 እግዚአብሔርም ከእነዚህ ወራሪዎች የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሣ፤ 17 እስራኤላውያን ግን ሌሎችን አማልክት ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንታቸውን አልሰሙም። አባቶቻቸው እግዚአብሔርን በመታዘዝ በሄዱበት መንገድ ሳይሆን፣ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሕግ በመከተል ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ። 18 እግዚአብሔር መሳፍንትን ባሰነሣላቸው ቍጥር ከመስፍኑ ጋራ ስለሚሆን፣ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ይራራላቸው ነበር። 19 መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር። 20 ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፤ “ይህ ሕዝብ ለቀደሙ አባቶቹ የሰጠሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፈ፣ እኔንም ስላልሰማ፣ 21 ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው በምድሪቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንዳቸውንም እንኳ በፊታቸው አሳድጄ አላስወጣም። 22 ይህን የማደርገውም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣ እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን መንገድ የሚጠብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ እፈትናቸው ዘንድ እነርሱን መሣሪያ ለማድረግ ነው።” 23 ስለዚህ እግዚአብሔር እነዚያን ሕዝቦች በዚያው እንዲኖሩ አደረገ፤ በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት ወዲያውኑ አሳድዶ አላስወጣቸውም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.