መሳፍንት 18 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምዳናውያን ሰዎች በላይሽ ሰፈሩ 1 በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም። የዳን ነገድም በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስተ ድርሻውን ገና ስላልወሰደ፣ የሚሰፍርበትን የራሱን ርስት ይፈልግ ነበር። 2 ስለዚህ ዳናውያን ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ ዐምስት ኀያላን ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ከተሞች ወደዚያ ላኩ፤ እነዚህም ነገዶቻቸውን ሁሉ የሚወክሉ ነበሩ። የላኳቸውም ሰዎች፣ “ሂዱ፤ ምድሪቱን ሰልሉ” አሏቸው። መልእክተኞቹም ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር ገቡ፤ ወደሚያድሩበትም ወደ ሚካ ቤት መጡ። 3 በሚካ ቤት አጠገብ እንደ ደረሱም የወጣቱን ሌዋዊ ድምፅ ዐወቁ፤ ስለዚህ ወደዚያ ጐራ ብለው፣ “ወደዚህ ያመጣህ ማን ነው? እዚህ ምን ትሠራለህ? የመጣኸውስ ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 4 እርሱም፣ “ሚካ ይህን አደረገልኝ፤ ቀጠረኝ፤ ካህኑም ሆንሁ” አላቸው። 5 እነርሱም፣ “መንገዳችን መቃናት አለመቃናቱን እንድናውቅ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት። 6 ካህኑም፣ “በሰላም ሂዱ፤ መንገዳችሁን እግዚአብሔር አቃንቶላችኋል” ብሎ መለሰላቸው። 7 ስለዚህ ዐምስቱ ሰዎች ከዚያ ተነሥተው ወደ ላይሽ መጡ፤ ሲዶናውያን ያለ ሥጋት በጸጥታ እንደሚኖሩ ሁሉ፣ በዚያም የሚኖረው ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር አዩ። ምድሪቱ አንዳች የሚጐድላት ነገር ባለመኖሩ ሕዝቡ ባለጠጋ ነበር። እንዲሁም ከሲዶናውያን ርቆ የሚኖር ሲሆን፣ ከማንኛውም ሕዝብ ጋራ ግንኙነት አልነበረውም። 8 ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል እንደ ተመለሱ ወገኖቻቸው፣ “የሄዳችሁበት ጕዳይ እንዴት ሆነ?” በማለት ጠየቋቸው። 9 መልእክተኞቹም እንዲህ አሏቸው፤ “ምድሪቱ እጅግ መልካም መሆኗን አይተናል፤ እንግዲህ ተነሡ! ሄደን እንዋጋቸው፤ ተነሡ እንጂ ዝም ትላላችሁን? ወደዚያው ሄዳችሁ ምድሪቱን ለመያዝ አታመንቱ፤ 10 እዚያ ስትደርሱም በመተማመን የሚኖር ሕዝብ፣ እግዚአብሔር በእጃችሁ የሚሰጣችሁን አንዳች ነገር ያልጐደላትን ሰፊ ምድር ታገኛላችሁ።” 11 ከዚያ በኋላም ከዳን ወገን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ። 12 ወጥተውም በይሁዳ ምድር ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ እንግዲህ ከቂርያትይዓይሪም በስተ ምዕራብ ያለው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር መባሉ ከዚሁ የተነሣ ነው። 13 ከዚያም ተጕዘው ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር በመሄድ ወደ ሚካ ቤት መጡ። 14 የላይሽን ምድር ሰልለው የነበሩት ዐምስቱ ሰዎች ለወንድሞቻቸው፣ “ከእነዚሁ ቤቶች በአንዱ ኤፉድ፣ ተራፊም፣ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ዕወቁበት” አሏቸው። 15 ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጐራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት። 16 ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር። 17 ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋራ በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፣ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን ዐምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ። 18 እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፣ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው። 19 እነርሱም፣ “ዝም በል! አንዲት ቃል እንዳትተነፍስ፤ ከእኛ ጋራ ሁን፤ አባትም ካህንም ሁነን፤ ለአንተስ የአንድ ቤተ ሰብ ካህን ከመሆን ይልቅ በእስራኤል የአንዱ ነገድና ጐሣ ካህን ሆነህ ማገልገሉ አይሻልህምን?” አሉት። 20 ይህም ካህኑን ደስ አሠኘው፤ እርሱም ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና የተቀረጸውን ምስል ይዞ ከሕዝቡ ጋራ ሄደ። 21 እነርሱም ሕፃናታቸውን፣ የከብቶቻቸውን መንጋና ሀብታቸውን ሁሉ ወደ ፊት በማስቀደም ተመልሰው ሄዱ። 22 ከሚካ ቤት ጥቂት ራቅ እንዳሉም፣ የሚካ ጎረቤቶች ለርዳታ ተጠርተው ተሰበሰቡ፤ የዳን ሰዎችንም ተከታትለው ደረሱባቸው። 23 ከበስተኋላቸው ሆነው ሲጮኹባቸውም፣ የዳን ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው ሚካን፣ “ሰዎችህን ለውጊያ አሰባስበህ መምጣትህ ምን ሆንህና ነው?” አሉት። 24 እርሱም፣ “እንዴት፣ ‘ምን ሆንህ’ ብላችሁ ትጠይቁኛላችሁ? የሠራኋቸውን አማልክቴንና ካህኔን ወስዳችሁ ሄዳችኋል፤ ምን የቀረኝ ነገር አለ?” አላቸው። 25 የዳን ሰዎች፣ “አትሟገተን፤ አለዚያ የተቈጡ ሰዎች ጕዳት ላይ ይጥሉሃል፤ አንተም ቤተ ሰብህም ሕይወታችሁን ታጣላችሁ” አሉት። 26 የዳን ሰዎች ይህን ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም የማይችላቸው መሆኑን በማየት ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። 27 ከዚያም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ካህኑን ወስደው ወደ ላይሽ በመሄድ፣ በሰላምና ያለ ሥጋት ይኖር የነበረውን ሕዝብ በሰይፍ መቱት፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሏት። 28 የሚኖሩት ከሲዶና በጣም ርቀው ስለ ነበርና ከማንም ጋራ ግንኙነት ስላልነበራቸው የሚታደጋቸው አንድም አልነበረም፤ ከተማዪቱም የምትገኘው በቤትሮዓብ አጠገብ ነበረ። የዳንም ሰዎች ከተማዪቱን እንደ ገና ሠርተው መኖሪያቸው አደረጓት። 29 ከተማዪቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሯት፤ ቀድሞ ግን ስሟ ላይሽ ይባል ነበር። 30 እዚያም የዳን ሰዎች ለራሳቸው ጣዖታት አቆሙ፤ የሙሴ ልጅ፣ የጌርሳም ልጅ ዮናታንና የእርሱም ልጆች ምድሪቱ እስከ ተማረከችበት ጊዜ ድረስ ለዳን ነገድ ካህናት ሆኗቸው፤ 31 ስለዚህም ሚካ የሠራቸውን ጣዖታት፣ የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ባለማቋረጥ አመለኳቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.