መሳፍንት 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሚካ ያሠራቸው ጣዖታት 1 ሚካ የተባለ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር ሰው ነበር። 2 እናቱን፣ “አንድ ሺሕ አንድ መቶ ሰቅል ብር ተሰርቆብሽ፣ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼሽ ነበር፤ ብሩ ከእኔ ዘንድ ይገኛል፤ የወሰድሁት እኔ ነኝ” አላት። ከዚያም እናቱ፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለችው። 3 አንድ ሺሕ አንድ መቶውን ሰቅል ብር በመለሰላት ጊዜ እናቱ፣ “ብሬን የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት ለማበጀት ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተው መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው። 4 ስለዚህ ብሩን ለእናቱ መለሰላት፤ እናቱም ከላዩ ሁለት መቶ ጥሬ ብር ወስዳ ለብር አንጥረኛ ሰጠች፤ አንጥረኛውም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት አደረገው፤ ምስሎቹም በሚካ ቤት ተቀመጡ። 5 ሚካ የተባለው ይህ ሰው የአምልኮ ስፍራ ነበረው፤ አንድ ኤፉድና ተራፊም ሠርቶ ከልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው አደረገ። 6 በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። 7 በይሁዳ ምድር፣ በይሁዳ ነገድ መካከል በቤተ ልሔም የሚኖር አንድ ሌዋዊ ወጣት ነበር። 8 ይህም ሰው ሌላ መኖሪያ ስፍራ ለመፈለግ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ለቅቆ ሄደ። በሚጓዝበትም ጊዜ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ወዳለው ወደ ሚካ ቤት መጣ። 9 ሚካም፣ “የየት አገር ሰው ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔ በይሁዳ ምድር ከምትገኝ ከቤተ ልሔም የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፤ መኖሪያ ስፍራ እፈልጋለሁ” አለው። 10 ሚካም፣ “እንግዲያውስ ዐብረኸኝ ተቀመጥ፤ አባትም ካህንም ሁነኝ፤ እኔም በዓመት ዐሥር ሰቅል ብር እንዲሁም ልብስና ምግብ እሰጥሃለሁ” አለው። 11 ስለዚህ ሌዋዊው ዐብሮት ለመኖር ተስማማ፤ ወጣቱም ለሚካ ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። 12 ሚካም ሌዋዊውን ካህን አድርጎ አስቀመጠው፤ ወጣቱም ካህኑ ሆነ፤ በቤቱም ኖረ። 13 ሚካም፤ “ይህ ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ፣ እግዚአብሔር በጎ ነገር እንደሚያደርግልኝ አሁን ተረዳሁ” አለ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.